የህልሜ ጓደኛ 2
(ከክፍል 1 የቀጠለ...)
የሳምንቱን ቀናት በሙሉ በስራ ነው የማሳልፈው፡፡ ሰው ሳደርስ ሰው ስመልስ፡፡ ቢሆንም ግን የሰንበት ቀናት አልፈው ሰኞ ሲመጣ እኔም ልክ ሁለት ቀን እረፍት እንደቆየ ሰራተኛ ሁሉ በሞራል እና በወኔ አዲስ ሰው ሁኜ ለስራ እነሳለሁ፡፡ የመንግስት ሰራተኛው ቅዳሜና እሁድን እረፍት አድርጎ ሰኞን በአዲስ መንፈስ ሲቀላቀል እኔ ምንም እረፍት ሳይኖረኝ ሁሌም ልክ እንደ ሰራተኞች በአዲስ መንፈስ ነው የምቀበለው፡፡ ዛሬ ግን ሰኞ አስቀየመኝ፡፡ እንደ ድሮው በአዲስ መንፈስ ልቀበለው ተዘጋጅቼ ወደ ባጃጅ ሽቀላየ ስወጣ እሱ ግን ፊቱን አጨፈገገብኝ፡፡ የስራ መንፈሴን አቆሸሸው፡፡ ፈረንጆች ሰኞን ‹‹ብላክ መንደይ/ጥቁሩ ሰኞ/›› ይሉታል ሲባል ከሰኞ ጋር የቆየ ቂም ይኖራቸው ይሆናል እላለሁ፡፡ ምናልባት ፋሽስት ጣሊያን በሃብሻ አርበኞች ድባቅ የተመታበት ሰኞ ቀን ቢሆንስ? ለዚያ ይሆናል ሰኞን የሚጠሉት፡፡ እኔ ግን እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ሰኞን ከማክሰኞና ከቅዳሜ ለይቸ አላየውም- ያው እንደ ሌሎች ቀናት ሰኞም ቀን ነው፡፡ ሰኞም ባጃጅ ላይ እሰራለሁ፤ ማክሰኞም፣ ረቡዕም፣ አርብም… ወ.ዘ.ተ እንደተለመደው፡፡ ዛሬ ብቻ ነው ሰኞ ጥቁር የሆነብኝ ‹ብላክ መንደይ›! ጠዋት እንደተለመደው እንጀራ ፍርፍር ሰርቼ ቁርስ አድርጌ ልወጣ ሽንኩርት ከትፌ፣ ዘይት ጨምሬ ልክ በርበሬ ልጨምር ስል መብራት ድርግም አለ፡፡ ምን አለበት በርበሬ እስክጨምር ድረስ እንኳን ቢታገሰኝ? ይኸው የዛሬን ሰኞ ሳልፈልግ ለመፆም አቋም ያዝኩ፡፡ በቀጥታ ወደ ባጃጅ ስራየ በመግባት በመስመር ወረፋ ጠብቄ አራት ያህል ቢያጆ ከመስራቴ ባጃጄ መንገድ ላይ ተንተፋትፋ ቆመች፡፡ እንደ ዛሬ አማርሬ አላውቅም፡፡ በቃ ሰኞን ጠላሁት… black Monday ብቻ ሳይሆን የሆነ ‹የሰይጣን ቀን› መስሎ ይታየኝ ጀመር /የሰይጣን ቀን ግን ምን አይነት ነው?/ በዚህ የጭንቅ ሰዓት ነው ሳሮን የደወለችልኝ፡፡ ሳሮን ‹‹በእሱ ላይ የተጋረደውን የሰኞ ጥላሸት ገነጣጥለሽ ምሰኪኑን ብላቴና ነፃ አውጭው!›› ተብላ ከሆነ አካል የተላከች ነፃ አውጭ ወታደር መስላ ታየችኝ፡፡ ድምጿ የሰኞን የድብርት ጋግርት ብቻ ሳይሆን ሰማይ ላይ የተደገነውን ደመና ሳይወድ ያሸሻል፡፡ የሷ ድምፅ እንኳን ሰኔና ሰኞ ለተባበሩበት እንደኔ አይነቱ ምስኪን ይቅርና ለጤነኛዉም ቢሆን የሩፋየልን ጸበል ያስታዉሳል፡፡ ህፃናቱ ልብስ አውልቀው እርቃናቸውን የሚያርከፈክፋቸውን ቅዱስ ዝናብ፡፡ ሩፋኤል አሳድገኝ እያሉ የሚቦርቁበትን ካፊያ፡፡ የእሷ ድምጽ ለመንፈስም ለስጋም ምግብ ነገር ነው፡፡ ድህነቱን እያሰበ በተስፋ መቁረጥ መንፈስ የሚዳክርን ሰው ለጊዜዉም ቢሆን ከደዌውም ከድህነቱም ይፈውሰዋል፡፡ ደስታን አጎናጽፎ ቀኑን ያደምቅለታል፡፡ አልፎ ተርፎም ግለሰባዊ የእድገት ድጅት ያስቆጥረዋል፡፡ ‹‹አንተ ደነዝ!…›› አለችኝ ፍዝዝ ብየ ቀጥላ የምታወራዉን እየጠበቅሁ ሳለ፡፡ ተመልከቱ እንግዲህ ከስድቧ ጋር ሳቋ ሲጨምር፣ እኔን ለመግደል የተላከ የሚመስል ሳቅ… እንዴት በስድብ እያቀመሰችኝ አብሪያት እስቃለሁ? ይችን ልጅ ‹ገድሎ ማዳን› ዘይቤ ነገር ናት ልበል? ስንተኛ ክፍል እያለሁ ነበር ስለ ዘይቤ የተማርኩት? የሆነ ጊዜ ላይ መምህራችን ስለ ዘይቤ ሲያስተምሩን፡- ‹‹ይሄ እንቶኔ ዘይቤ ነው፣ ይሄኛው ሰውኛ ዘይቤ ይባላል፣ ይህኛው ደግሞ...›› ይሉንና አያይዘው ለዘይቤዎች ሁሉ ምሳሌ ይነግሩናል፡፡ ‹‹…ቀጣዩ የዘይቤ አይነት ደግሞ…›› አሉን ጋሽ ደግሰው ‹‹ቀጣዩ ደግሞ…›› ካሉን በኋላ ከጥቁር ሰሌዳው ጋር ሊያገናኙት የነበረውን ጠመኔ እንደያዙ ወደኛ ዞረው ከመሃል ወንበር የሚቀመጠውንና እረባሹን የክፍላችን ተማሪ በለጠን አፈጠጡበት፡፡ በተለይ በለጠ በጋሽ ደግሰው ክፍለ ጊዜ እረብሻው ይብስበታል፡፡ ከወንበር ወንበር እንደ ጦጣ ይዘላል፤ ደስ ሲለው አመር ብሎ ወጥቶ ወደ ጨዋታው ይፈተለካል፡፡ በዚህ ምክንያት ጋሽ ደግሰው ወላጅ ቢያስመጡትም የበለጠ አባት ከልጃቸው የባሰ ረባሽ ሆነው አረፉት፡፡ ይባስ ብለው ‹‹…ወንድ ልጅ ካልፎረፈ ምኑን ተማረው፣ አቦ! ደስ ካለው ይማር ደስ ካላለው ይውጣ… ህገ-መንግስቱ የፈቀደልንን የመንቀሳቀስ ነፃነትማ እናንተ ልትነፍጉት አይገባም…!›› ብለው ምስኪኑን ቲቸር ደግሰውን በተማሪዎች ፊት ሰድበዉትና አዋርደዉት ወጡ፡፡ ከትምህርት ቤት ተለቀን ወደ ቤታችን እየሄድን እያለ የበለጠ ሰፈር ልጆች ሲያወሩ እንደሰማሁት የበለጠ አባት እጅግ ሲበዛ ነጻነት ፈላጊ ናቸው አሉ፡፡ በየሄዱበት ሁሉ ነጻነት ነጻነት ማለት ያዘወትራሉ፡፡ እንዲያዉም ሁለቱ ትላልቅ ሴት ልጆቻቸው ከአባታቸው የተሰጣቸውን ነጻነት ተጠቅመው በተመሳሳይ ሰዓት ከተለያዩ ሾፌሮች ጋር ኮብልለው ልጅ ወልደው ተመልሰዋል አሉ፡፡ የበለጠ አባት በተማሪዎች ፊት ቲቸር ደግሰውን ካሸማቀቋቸው በኋላ ጋሽ ደግሰው በአባቱና በበለጠ ላይ ቂም ቋጥረው ነበር፡፡ ለዚያም ነው ሁሌም ክፍላችን ሲገቡ በለጠን ጥያቄ የሚጠይቁት፡፡‹‹በለጠ ይሄንን ሞክር እስኪ...›› ጋሽ ደግሰው ጠመኔ የያዘ እጃቸውን እያራገፉ በለጠ በብዛት ወደሚቀመጥበት ወንበርና ጠረንጴዛ ተመለከቱ፡፡ በለጠ ግን በሌላ አቅጣጫ ሆኖ በንቀት ድምፁን አጥፍቶና አድፍጦ ቁጭ አለ፡፡ ‹‹የታባቱ ሄዶ ነው ይሄ የንፍጣም ልጅ?›› ቲቸር ደግሰው በለጠ በሌለበት ንዴታቸውን ሊወጡ ነበር፤ በለጠ ግን ‹‹አቤት! ጠሩኝ መምህር›› አለ፡፡ /አንዳንድ ጀሮዎች ክፉዉን እንጂ ጥሩዉን አይሰሙም፡፡ ለዛ ይመስለኛል አብዛኛዉን እድሜያችንን ከምንግባባው ይልቅ የማንግባባበት የሚጎላው እላለሁ ዛሬ ሆኜ ሳስታዉሰው/ ያን ጊዜ ቲቸር ደግሰው ከመካከላችን ቆመው ፊታቸው በላብ ሲወረዛ አየኋቸው፡፡ ደግሞ እንዴት እንደደነገጡ፤ ሲያሳዝኑ፡፡ ‹‹በለጠ›› ሲሉ ጠሩት፡፡ ‹‹አቤት መምህር›› አለ ከመቀመጫው እየተነሳ ‹‹የንፍጣም ልጅ! ማለት ስድብ ሳይሆን የዘይቤ አይነት ነው›› አሉ መምህር ደግሰው ከፊት ለፊታቸው የቆመውን በለጠን እያዩ፡፡ ‹‹ይሄ ደግሞ ምን የሚሉት ዘይቤ ነው ቲቸር?›› በለጠ የመጥፎው ጊዜ ጀሮው መስማቱ ብቻ ሳይሆን ጥያቄ ጠያቂ መሆኑ ብዙዎቻችንን አስገረመን፡፡ ‹‹ገድሎ ማዳን ይባላል… ገድሎ ማዳን ዘይቤ!!›› ብለዉት አረፉ፡፡ በሳምንቱ አማርኛ ፈተና ስንፈተን ከቀረቡልን ጥያቄዎች መካከል አንዱ እንዲህ የሚል ነበር ‹‹የገድሎ ማዳን ዘይቤ ምሳሌ ጥቀሱ›› ከፈተና ስንወጣ መቀለድን ‹‹አጭር መልስ ስጥ የሚለዉን ምን ብለህ ሞላኸው?›› አልኩት፡፡ ‹‹የገድሎ ማዳን ዘይቤ ምሳሌ ጻፉ የሚለውን ነው?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡ ‹‹አዎ›› ‹‹እሱማ ቀላል ነው፤ መልሱ የንፍጣም ልጅ ነው!›› አለኝና እንባየ እስከሚፈስ አሳቀኝ፡፡ **** ሳሮንን የሆነ ቀን ወደ ቤቷ እየሸኘኃት እያለ አንድ ቀን ላይ አባቷን እንደምታስተዋውቀኝ ነገረችኝ፡፡ ጠላታችሁ ክው ይበልና ባለሁበት ደርቄ ቀረሁ፡፡ እራሴው የማሽከረክራትን ባጃጅ አላመንኳትም፡፡ ዳክየ የምታክል ባጃጄ የሆነ የወታደር ኦራል መኪና ሆና ታየችኝ፡፡ ትንንሽ ጎማዎቿ ወደ ሰንሰለት ጎማ ተለወጡ… ኦራሉ ተራራ ነሽ፣ ገደል ነሽ፣ ወንዝ ነሽ፣ ዛፍና ድንጋዩን ሁሉ እየገነጣጠለ ሲሄድ በህሌናየ ታየኝ፡፡ የሆነ የቀን ህልም ዉስጥ ገባሁ፡፡ ከባዱን ኦራል መኪና ሳሮን ራሷ ወደቤታቸው ትነዳዋለች፡፡ እኔ እስረኛ መስየ ከመሀል ወንበር አካባቢ ያለሁ ይመስለኛል፡፡ ግራና ቀኝ ፊታቸው የማይታይ የተሸፋፈኑ ኮማንዶ ወታደሮች በሆነ ምትሀት እንዳላመልጣቸው በተጠንቀቅ ይጠብቁኛል፡፡ ኦራሉ ይበራል፡፡ ከሆነ ጫካ የከበበው ግቢ ሲደርሱ ወታደሮቹ ተረባርበው ከኦራሉ ያወርዱኛል፡፡ ፊት ለፊት የሳሮን አባት የዱር አንበሳ መስለው… የሆነ የተቆጣ ነብር መስለው… የተራበ ጅብ መስለው ቁመው ሲያፈጡብኝ ይታየኛል፡፡ ሁለቱ የተሸፋፈኑ ሰዎች /የጋኔል ወንድሞች/ ግራና ቀኝ እጄን ይዘው ልክ መላእክት ከዙፋኑ ላይ ወዳለው ፈራጅ አንድን ነፍስ እንደሚወስዱት አድርገው የሳሮን አባት ፊት ሲገትሩኝ የሳሮን አባት በጋለ ትንፋሽ ፣በፈጠጠ አይን፣ በተቆጣ ሰውነት የጥያቄ መአት ያወርዱብኝ ጀመር፡፡ ‹‹አንተ ማን ነህ?›› ‹‹እ… እኔ… እንጃ… እኔ ማን ነኝ?›› ‹‹ስራህ ምንድን ነው?›› ‹‹የባጃጅ ሹፌር… የቀን ሰራተኛ… በቀን መቶ ብር የሚከፈለኝ›› ሃሃሃሃሃሃ… ረጅም ሳቅ… ‹‹…እና አንድ መናጢ ደሃ!… ምናምንቴ!… የምናምንቴ ልጅ! ከኔ ልጅ ጋር ምን አባህ አገናኘህ?›› ‹‹እድል… መጥፎ እድል… አጋጣሚ… እ…›› የሳሮን አባት ደማቸው ይፈላና እኔን ማየት እያንገሸገሻቸው ትእዛዝ ያስተላልፋሉ፡፡ የማይሻር ትእዛዝ…. ቀኝ እጃቸውን ከአንገታቸው ላይ አስቀምጠው ከግራ ወደ ቀኝ ይሰርዙታል፡፡ ‹‹እ.ረ.ዱ.ት!›› ‹‹ዋ…ይይ!›› ብየ ከመቀመጫየ ተነስቼ መሪዉን ለቅቄ ልሮጥ ሲያምረኝ ሳሮን ከጀርባ ሁኔታየን አይታ እንቅ አደረገችኝ፡፡ ደግነቱ ሞተር ማጥፋቴ እንጂ ከሌላ ተሸከርካሪ ጋር መላተሜ የማይቀር ነበር፡፡ ‹‹ምነው አንተ ሞዛዛ?… አባቴን ላስተዋውቅህ ስልህ ተቀያየርክ?›› ‹‹እ… ምንም! ኧረ ምንም! ብቻ አባትሽ…›› ቅዠቴን ብናገር አንድ አመት እንደምትስቅብኝ ስለማውቅ መናገር ነፈግኳት፡፡ ‹‹…የምር ግን ባስተዋውቅህ ይደብርሀል? አባየኮ ምርጥ ሰው ነው፡፡ ሰው አክባሪ፣ ጨዋታ የሚወድ፣ ሁሉን ሰው በአንድ አይን የሚያይ፣ የሰውን ሀሳብ የሚረዳ፣ በቃ አባየን እንዴት ልግለፅልህ? አባየ ከዚህ በላይ ነው›› ‹‹ማርያምን በይኝስኪ›› እጇን ጥብቅ አድርጌ ያዝኩና አይኗን በስስት አየኋት፡ ‹‹ማርያምን!›› በግራ እጇ የግራ እጄን መዳፍ ይዛ በቀኝ እጇ ሌባ ጣት መዳፌ ላይ የመስቀል ቅርፅ ሰርታ ማለችልኝ፡፡ አላመንኳትም፡፡ ይች ልጅ ልታሳርደኝ ነው እንዴ? እነዚያ የጋኔል ቁራጮችስ?፣ ግቢ የሚጠብቁት ወታደሮች፣ በቅዠቴ እጄን ጠምዝዘው የወሰዱኝ ጠባቂዎች፣ የአባቷ የተቆጣ ሰውነት፣ ይህ ሁሉ በቲቪ እንደማየው እግር ኳስ ጨዋታ በምናቤ ሽው እልም ይልብኝ ጀመር፡፡ ‹‹ታዲያ የቅድሙ ሰው ማን ነው?›› ጠየቅኋት ‹‹የትኛው?›› ‹‹ይቅርታ! ለካ አንች አላየሽዉም ቅዠቴ ነው፤ እኔ የሳልኩትን የቅዠት ገፅ ባህሪ አንች እንዴት ልታይው ትችያለሽ? ለካ ህልማችንን ሌሎች አያዩትም፡፡ ህልም እና ራዕያችንን አይቶ የሚደግፈን ቢኖር ኑሮ የት እንደርስ ነበር፡፡ ግና አልመን ህልማችን መልስ አልባ ሆኖ ይቀራል፡፡ ህልማችንን ከሚጋራን ይልቅ የሚያደናቅፈን ይበዛል፡፡ በዚች አገር እንዳየሁት ህልምና ራዕይ እዉን የሚሆነው መፈክር ላይ ብቻ ነው፡፡ ‹‹አቅዱ›› የሚለን እንጂ እቅዳችንን የሚያለመልም አካል የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ሃሳባችንን፣ ህልማችንንና እቅዳችንን ታቅፈን በቅዠት የምንዳክረው፡፡ ህልም ተግባር ካለሆነ ምንም ዋጋ የለውም? እቅዳችን ዉጤት አልባ ከሆነ ምን እቅደ ሆነ? ለዚያ ይመስለኛል የተዘቀዘቀው ሳይቃና… የወደቀው ሳይነሳ… በወደቀበት የሚቀረው፡፡ በጎ ህልም ተግባር ከሌለው በቀጥታ ወደ ቅዠት ይቀየራል፡፡ ‹‹ሳሮንየ… አባትሽ ግን አንቺንና እኔን በአንድ ላይ ቢያዩን አይቆጡም?›› ‹‹ውይ! አባየ ነው የሚቆጣ? አባቴ ሰው ሲወድኮ… እንኳን ከኔ ጋር ሆነህ ብቻህን ቤታችን ብትሄድም አባየ ሰው ያምናል፤ ባለስልጣን አይመስልም፡፡ በራሱ ስለሚተማመን ሰውን የሚያስበው በራሱ ደግነትና የዋህነት ልክ ነው፡፡ አባየ ልቡ የሴት ልብ በለው፤ እኔንኮ እንደ እናትም እንደ አባትም ሁኖ ነው ያሳደገኝ፡፡ የግቢው ጠባቂዎች ‹‹ይሄ መንገድ ለእርስዎ ያሰጋል፤ በዚህ አካባቢ አይንቀሳቀሱ›› ቢሉትም አይሰማቸውም፡፡ ‹‹እኔ ህዘቤን የምወድ፣ ያለኝን የማካፍል፣ የህዝብን ሀብት የማልመኝ፣ ህመሙ የሚያመኝ፣ ዉድቀቱ የሚቆረቁረኝ የስጋ ወንድሙ እንጂ ጠላቱ አይደለሁ›› ይላቸዋል፡፡ እነሱ ግን ‹‹የበላይ ትዕዛዝ ነው›› ብለው አባየ ወክ ሲያደርግ በሩቅ ርቀት በመሳሪያ ያጅቡታል፡፡ እሱ ግን አይፈልጋቸውም፡፡ ‹‹ጎሊያድ ብረት ለበሱን ባለ ወንጨፉ ዳዊት በአንድ ጠጠር እንደጣለው ማን በነገራችሁ›› ይላቸዋል፡፡ አንዳንዴ ቴሌቪዥን ላይ የአፍሪካን ዜና ስናይ አባቢ ከዉስጡ ሲያዝን አስተዉለዋለሁ ‹‹እስከመቼ ይሆን ለህዝብ ጥያቄዎች ሁሉ መልሱ ጠመንጃ የሚሆነው? አይ እማማ አፍሪካየ…›› ይላል፡፡ ‹‹በቃ! የምር ሴት ነገር በለው… የሴት ልብ! አይ አባቢ… የኔ ዉድ አባት፤ስወደዉኮ›› ብላ አይኖቿን ጭፍን አድርጋ በሃሳብ አባቷ ጋ ጭልጥ ትላለች፡፡ ያኔ አጠገቧ ሆኜ ሙዝዝ ብየ እየተመለከትኳት ‹‹ምንአለበት አንዴ አይኗ ሳይገለጥ ከንፈሯን…!›› /በስመአብ ርኩስ መንፈስ ከኔ ራቅ/ ‹‹ሳሮኔ! አባትሽ ባለስልጣን ሆነው ሳለ እንዴት እንደዚህ ደግና የዋህ ሆኑ?›› አልኳት አንዳንድ ስግብግብ ባለስልጣናት በህሌናየ ሲመጡብኝ፡፡ ‹‹ሲሳይ- ባለስልጣን መሆን ደግ ከመሆን አያግድም፡፡ አባቴ ባለስልጣን ከመሆኑ በፊትም በኋላም ያው ሰው ነው፡፡ ባለ ስልጣንን ክፉም ደግም አድርገን እንድናሰስብ የሚያደርገን የፓለቲካ ምህዋሩና የእኛ አስተሳሰብ (አመለካከት) ነው፡፡ አሁን እኔ ስለ አባቴ ባልነግርህ አንተ ሁሌ አባቴን ቆራጭ ፈላጭ አድርገህ ነበር የምትመለከተውና የምታስበው›› ‹‹በጣም!›› አልኩኝ በልቤ… (አንገቴን ሲያስቆርጠኝ በቅዠቴ ያየሁት ዳግም እየታየኝ) ‹‹ግን አባቴ እንደዛ አይነት አይደለም፤ እንዳልኩህ ሁሉም ስልጣን ላይ ከመሆኑ በፊት ተራ ሰው ነበር፡፡ በርግጥ ሰው ከሰው ይለያያል፡፡ ክፉም ደግም መሪ አለ፡፡ ደጉ መሪና ባለስልጣን የህዝብ ለቅሶ የሚያስለቅሰው፣ የህዝብ ርሀብ የሚርበው፣ ጀግንነቱ ወኔ… ሽንፈቱ ሞት የሚሆንበት ብልህና አስተዋይ ነው፡፡ የሀገሩን መሬት ዳር ድንበር ይቅርና አፈሯ በነፍስ ስትወሰድ የሚቆጨው፣ ሁሉም ሃላፊ ጠፊ መሆኑን አምኖ የሚያገለግል፣ የህዝቡን አስተሳሰብ ከልቡ የሚረዳ ቅን፣ለችግሮች መፍትሄ የሚያፈላልግ ነው፡፡ ጨካኙ መሪ ደግሞ የህዝብ ደስታና ሳቅ የሚያንገፈግፈው፣ ለቅሶው የሚናፍቀው፣ ሀገሩን ለገንዘብ የሚሸጥ፣ ጠላትን መንገድ መርቶ፣ መሬት ቆርሶ የሚሸጥ ባንዳ ይሆናል፡፡. አባየ ግን…›› ንግግሯን የሆነ ዉጣዊ ስሜት ሲገታት በአይኔ በብረቱ ተመለከትሁ፡፡ ሳሮን ስትናገር የሆነ መንፈሳዊ ስብከት የምሰማ እንጅ ከአንዲት ወጣት ሴት የሚወጣ ቃል አይመስለኝም፡፡ ንግግሯ ወደ ውስጤ ነው የሚዘልቀው፡፡ ውዳቂ የለውም፡፡ እና የምትናገረዉን ሁሉ አንዳች ሳልጠራጠር አምናታለሁ፡፡ በቃ! ሁሉም እዉነት ነው፡፡ ከፊት ለፊቴ ተቀምጣ አይኗን ክፍት ክድን እያደረገች ከተመለከተችኝ በኋላ- “ደግሞ… እራሱ አባቴ ነው ይዘሽው ነይና አስተዋወቂኝ ያለኝ… ሁሉንም ነገር ነግሬዋለሁ” ‹‹ምኑን ነው የነገርሻቸው?›› ልቤ ከመሃሉ ላይ ለሁለት ክፍል ስትል ታወቀኝ፡፡ (ይቀጥላል....)
Comments
Post a Comment