የህልሜ ጓደኛ 1
ቤታቸው ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግስት የሚተናነሰው ጠቅላይ ሚንስተሩ እዚያው ባለመኖራቸው ብቻ ነው፡፡ ልጥጥ ያለች የባለሀብት ልጅ፡፡ ያውም የባለስልጣን፡፡ ግቢያችውን ላስተዋለው አንድን የተከበረ ጫካ በማን አለብኝነት ወርሰውና መሀሉን አስመንጥረው መኖሪያቸውን እዚያ የመሰረቱ ይመስላል፡፡
ከውጭ ሆኖ ለተመለከተው ግቢው የቤተ-ክርስቲያን ቅጽር ወይም የሆነ ፓርክ ይመስላል፡፡
ግቢውን ከከተማው አስፓልት የሚያገናኝ አንድ ጠበብ ያለ የአስፋልት መንገድ አለ፡፡ መንገዱ ከዋናው መስመር ይገነጠልና ከሁለት እሰከ ሶስት የሚሆኑ የሚያማምሩ ቤቶችን ካለፉ በኋላ ቀጥ ባለ አስፋልት ወደነ ሳሮን ቤት ያደርሳል፡፡ አሰፋልቱ ግራና ቀኝ በተተከሉና ቅጠላቸውን በታቀፉ ዛፎች መካካል የተዘጋ ነው፡፡ ማዶና ማዶ ያሉት ዛፎች ወዳጅነት መስርተው በአየር ላይ ቅርንጫፎቻቸውን አስተቃቅፈዋል፡፡
ውስጥ ለውስጥ በአስፋለት መንገዱ አብዛኛውን ጊዜ ሁለት መኪኖች ሽር እያሉ ይወጣሉ ወይም ይገባሉ፡፡ አንደኛው የአባቷ ፕራዶ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በብዛት እሷ የምትነዳው ራቫ ፎር፡፡ ከግቢው አጠገብ ዘበኛው አይጠፋም፡፡ ዘበኛው ማለት የሚከብድ ቢሆንም ያው ዘበኛ ስለሆነ ምንም ሊባል አይችልም፡፡ የሚያምር ጥቁር ጨርቅ ሱሪ ከነጭ ሸሚዝ ጋር ለብሷል፡፡ ካራቫት አላሰረም፤ የላይኞቹ ሁለት የሸሚዙ ቁልፎች አልተቆለፉም፡፡ የሸሚዙ ያለመቆለፍ ከአንገቱ ላይ ላንጠለጠለው የብር ሀብል የተመቸው ይመስል ሀብሉ ደረቱ ላይ ያብረቀርቃል፡፡
ዘበኛነቱን ያወቅሁት እንግዳ ሲመጣ በር ሲከፍትና መኪና ከወጣ በኃላ መልሶ በር ሲቆልፍ ነው፡፡ ልዩ የሆነ ስነ-ምግባር አለው፡፡ የሸሚዙን እጅጌ በሁለት ጊዜ ድግግሞሽ ወደ ላይ ቀንፎታል፡፡ ክንዱ አካባቢ ያለው የእጁ ዉፍረትና የሰፋው ደረቱ ላይ ማራኪ ባህሪው ታክሎበት በወታደራዊ ስነምግባር እና በአካል ብቃት እንቅስቃሴ የታነጸ ታማኝ ወጣት መሆኑን ለመገመት አይከብድም፡፡ ያንን ቁመትና አቋም ይዞ ሰው በወጣና በገባ ቁጥር ጎንበስ ቀና እያለ በፈገግታ የታጀበ ሰላምታ ይሰጣል፡፡ የሚወጣዉን በተስፋ ይሸኛል፡፡ በር ይዘጋል- በር ይከፍታል፡፡
ታደሰን ደግሞ አሰብኩት፡፡ ታዴ ሰፈራችን ካለው ብረት/ክብደት/ ቤት የብረት ክብደት ሲያነሳና ሲያወርድ ይኸው አምስተኛ አመቱን ደፈነ፡፡ በአጭር ቁመቱ ላይ ዉፍረቱ ታክሎበት ጃምቦ ቤት እንጂ ክብደት ቤት የከረመ አይመስልም፡፡ በዚያ ላይ ኩራቱ፣ መንጠባረሩ፣ ሴት ማስቸገሩ፣ ወንድ ልጅን መዝለፍና ማንገራገሩ አይጣል ነው፡፡
ይኸው ገልቱ ታደሰ ባለፈው ከእማማ ዘመናይ ጋር ተጋጨ፡፡ እግዚአብሄር ያሳያችሁ የሃያ አራት አመት ጎረምሳ ከሰባ አመት አሮጊት ጋር ምን አገናኘው? ቢቻለው መንገድ ቢመራቸውና ቢያግዛቸው እንጂ እንዴት ቁሞ ስድድብ ይገጥማቸዋል? ተብሎ በኛ ሰፈር ሰዎች ተረገመ፡፡ ‹‹ይቁረጥህ፣ በእጭር ይቅጭህ፣ ይቀንጥስህ፣ ወጣትነትህን አትጨርሰው…›› ተብሎ ተረገመ፡፡ ይሄንን ሁሉ ርግማን አልፎ ታዴን በማግስቱ አይኑን አየዋለሁ ብየ አልገመትኩም፡፡ እንዲያዉም የሰፈራችንን የእድር ጥሩምባ ነፊ ድምጽ ብቻ ነበር አብዛኞቻችን የምንጠብቀው፡፡ ‹‹ቱቱቱቱ…. እድርተኛ የሆናችሁ በሙሉ… ወጣት ታደሰ አካሉ ከዚህ አለም በሞት ስለተለየ እንድታላቅሱን ተብላችኋል›› የሚል ድምጽ ስንጠብቅ የጥሩንባ ድምጽ ቀርቶ ኮሽ የሚል ድምጽ ሳይሰማ ሌሊቱ በሰላም ነጋ፡፡ ከእርግማን ተርፎ በሰላም ማደሩን ለማረጋገጥ ጠዋት ወደ ቤቱ ፈጠንኩ፡፡ እርግማን ለታዴ ምርቃት ሆኖለት እንደገና ሰዉነቱ ለምልሞ ያየሁት መሰለኝ፡፡ ወዝ ደፍቶበታል፡፡
ረፋድ አካባቢ ታዴን ከእማማ ዘመናይ ጋር ያጋጨውን ጉዳይ ለማጣራት የኛ ሰፈር ሰዎች ወሬ ማነፍነፍ ጀመሩ፡፡ እማማ ዘመናይ ከጎረምሳ ጋር ምን አጋጨዎት? ተብለው ሲጠየቁ እንዲህ አሉ-
‹‹ሆሆ ይሄ ታደሰ የሚሉት ገልቱ ቤቴ ድረስ መጥቶ ‹‹አንቺ በሰፈሩ ተሰሚነት ያለሽ ሰው ነሽ፣ አንቺ ስትናገሪ ሁሉም ያምንሻልና የሰፈሩ ጉልቤ መሆኔን ለሁሉም አስወሪልኝ›› ብሎኝ እርፍ!›› እማማ ዘመናይ እየተብተከተኩ ለተሰበሰቡት ወጣቶች… ህጻናትና አዋቂዎች ተናገሩ፡፡ ‹‹አሁን ይቺን ክንድ ይዞ የሰፈሩ ጉልቤ ነኝ ሲል አያፍርም?›› አሉ፡፡
ከተሰበሰቡት መሃል አንድ ፍርሃት ያደረባት ኮረዳ ‹‹እና ምን አሉት እማማ ዘመናይ?›› ስትል ጠየቀች፡፡
‹‹እኔ ዘመናይ ነኝ ህዝብ የማሳምንለት? እንደ አቡነ ጴጥሮስ መስዋእትነትን እከፍላለሁ እንጂ፣ እንደ መንጌ አንድ ጥይት እስከምትቀር እታገላለሁ እንጂ… ያንተን ጉልቤነት ለሰፈራችን አልሰብክም አልሁታ!›› ብለው በወኔ ተናገሩ፡፡
እዉነት ለመናገር የነሳሮንን ዘበኛ አይቼ ከታደሰ ጋር ሳነጻጽረው ፈጣሪ የዘበኛዉን ክንድ ከሰራ በኃላ የተራረፈውን ቅንጥብጣቢ ስጋና አጥንት ገጣጥሞ ‹ታደሰ› የሚባል አንድ ገልቱ ፍጡር የሰራ ይመስለኛል፡፡
****
ሳሮን በመኪናዋ ከተማ መውጣት አይመቻትም፡፡ ነፃነቴን መገፈፍ አልፈልግም ትላለች፡፡ ደስ ሲላት በእግሯ መንቀሳቀስ፤ ካሻት ባጃጅ ተጋፍታ ሁለት ብር ከፍላ የፈለገችው ቦታ መድረስ ነው የሚያስደስታት፡፡ መኪና ስትነዳ ብቻዋን ናት፤ ማንም አያጫውታትም፤ ምንም አያስቃትም፤ ማንም አይፎግራትም በቃ ወና ነገር፡፡ ‹‹ደረስ መለስ የሆነ ህይወት ነው›› ትላለች መኪና ይዞ መንቀሳቀስን፡፡ ‹‹ባጃጅ ውስጥ ብዙ ወሬ አለ፣ መልስ ሲጠፋ በሃያ አምስት ሳንቲም ጭቅጭቅ አለ፣ ተሳፋሪና ሹፌር ንትርክ አለ፣ ጅንጀናና ቀልድ አለ፣ የሚያዋራህ ባኖር እንኳን የተለጠፉ አዝናኝ ጥቅሶችን እያነበብክ ብቻህን ታዘግማለህ፡፡ ታክሲና ባጃጅ ላይ ስትሳፈር ክፍል ውስጥ ክፍለ ግዜ ወጥቶለት የማትማረው የሆነ የህይወት ትምህርት አለ›› ወሬ ስትጀምር ሁሌም ይሄን ነው የምትናገረው፡፡
ሳሮን የናጠጠች የሀብታም ልጅ ናት፡፡ ደግሞ አባቷም ባለስልጣን ናቸው፡፡ ሀብታቸው የመጣው ከስልጣን በፊት ወይም በኃላ በእርግጠኝነት ባይታወቅም በጥቅሉ እንደሌሎች ሴቶች ግን አይደለችም፡፡ ሀብታም በሚሉት ገደል ውስጥ ተደብቃ ብዙ ነገር ማጣት አትፈልግም፡፡ የሷ ሀብቷ መዝናናት ነው፣ መጫወት፣ መጠጣት፣ ማጨስ ሰዓቷ ሲደርስ በማይታመን ፍጥነትና ባልተገመተ መንገድ ያንን የሞቀ ህይወት ሸውዳ ቤቷ መግባት፡፡ እንደ ቀላ መንደሪን ሊገምጧት የተዘጋጁ ወንዶችን በየት በኩል እንዳለፈቻቸው ሳያስተውሉ በዉበቷ ናዉዘው፣ አይናቸው እንደፈጠጠ፣ ሲጋራቸው ብቻውን እየጨሰ እሷ ግን ከመካከላቸው ላጥ ብላ ትጠፋለች፡፡ ወንዶቹ ሲጋራቸው ጭሱ አልቆ እሳቱ እጃቸውን ሲጠብሳቸው ነው የሚባንኑት፡፡ በዚያ ቅጽበት ወፏ ሳሮን ግን ቤቷ ገብታ ውሎዋን እያጣጣመች ነው፡፡ አልጋዋ ላይ፡፡
ብዙ ወንዶች አንዣበውባት አላገUትም፡፡ ባለሀብት ነን ባዮች… ሴት አታመልጠንም እያሉ የሚፎክሩ ወጣቶች… ቅሌታም ባለስልጣን ነን ባዮች… በአጠቃላይ በውበቷ ተማርከው ሊያማልሏት ከሞከሩት ይጀምርና በየመጠጥ ቤቱ ደስታዋን ሊያጨልሙት እስከሚሞክሩት ድረስ ሳሮንን ለማግኘት ያልተሸረበ ሴራ፣ ያልተሞከረ እርምጃ አልነበረም፡፡ ግን ሴራው ሴራ ብቻ ሁኖ ይከሽፋል፡፡ ያለምንም አድማ በታኝ፡፡ ያለምንም ኮማንድ ፖስት፡፡
ከተቀመጠችበት የባለጌ ወንበር ላይ ፊቷን ከጨፈገገችውና ሲጋራዋን ለኩሳ አንገቷን ደፍታ በንቀት መሬቱን መመልከት ከጀመረች ወዲያው ‹‹የሆነ ደባሪ ፊት… የሆነ ቀሽም ወንድ… ከጭንና ከጭን መካከል ብቻ የሚያስብ ጠርሙስ ጭንቅላት የሆነ ሰው›› አይታለች ማለት ነው እላለሁ፡፡
‹‹ሲሳይ…›› ስትጠራኝ ድምጽዋ ያስደነግጠኛል፡፡
‹‹ወየ… እናቴ… እህቴ… እመቤቴ›› ይሄ ሁሉ ስም የሚያረካት አይመስለኝም፡፡ ድምጿ የሆነ የድሮ ሙዚቃ ይመስለኛል፡፡ ዋሽንት፣ ከበሮ፣ በገና… ከዚያም ድምፃዊው በአንድ ላይ በፍቅር ተዋህደው የሚወጣው ነፍስ የሚዘራ ዜማ፡፡ /የአሁን ሙዚቃማ ኪቦርድና ኮምፒዩተር ብቻ አይደል እንዴ?/ አሉ ጋሽ ሽብሩ፡፡
‹‹ሲስየ እንውጣ በእናትህ…›› /በናትህ ማለት ለምን አስፈለገ?... እንዉጣ የሚለው ቃል ብቻኮ ከልክ በላይ በቂ ነው/ ቅንጣት ሳላመነታ እኔ ቀድሚያት እወጣለሁ፡፡ ወዲያው በብርሀን ፍጥነት ተከትላኝ ትወጣለች፡፡ ከሞቀው ጭፈራ ቤት ውልቅ በአንዴ፡፡
‹‹ሲሳይ ወደ ቤት አድርሰኝ?››
‹‹ምነው ደበረሽ ሳሮኔ? ሌላ መጠጥ ቤት አትቀይሪም?››
‹‹ሙዴን አበላሹት እነዚያ ቀሽሞች…›› እዚያ ጭፈራ ቤት ያየኋቸው ሳሮኔን ያስቀየሟት ወንዶች በህሌናየ ይመጣሉ፡፡ ገልቱዎች!
‹‹እሺ! አንቺ ካልሽ እንሂድ…›› እንደ ጭፈራ ቤት በመብራት የተንቆጠቆጠች ባጃጄን ሞተሯን አስነስቼ እያስጓራሁ አከንፋታለሁ፡፡ ወደነ ሳሮን ቤት፡፡ ግቢያቸው እንደደረስን ያ አመለ ሸጋ ወጣት የግቢያቸው ዘበኛ የግቢ በር ይከፍትላታል፡፡ ከባጃጄ ስትወርድ የሻከረ ጉንጬን በለስላሳ ከንፈሯ ሳም አድርጋኝ፣ እጇን አውለብልባልኝ፣ መልካም መአዛዋንና ትዝታዋን ብቻ ጥላልኝ ላጥ ትላለች፡፡ ያኔ በድን ሆኜ ከቆምኩበት ሳልንቀሳቀስ በአይነህሌናየ ሳሮንን ባየሁበት መነጸር ሌሎች የከተማችን ሴቶችን እቃኛቸዋለሁ፡፡ ለማስረጃነት የባጃጅ ደንበኞቼ የነበሩትን ኮረዳዎች ብቻ ማየት በቂ ነው፡፡
ኢሌኒ- ከተሳፈረችበት ቦታ ጀምሮ እስከምትደርስበት ድርስ ወሬ የሚባል ነገር አታወራም፡፡ ‹‹የት ድረስ ነው የምትሄጂው?›› ስላት እንኳን ቃል ከአፏ ለማዉጣት ስንት ደቂቃ ተለምና ነው፡፡ ‹‹እግዚያብሄር ይሄን የመሰለ ዉበትና አቋም ለግሷት እንዴት ጸባይ ይነሳታል?›› እላለሁ ለብቻየ፡፡
የሄለን ደግሞ ይባስ፡፡ የአገልግሎቴን ክፍያ ለመክፈል ከቦርሳዋ ገንዘብ አዉጥታ እጄ ላይ ለማስቀመጥም ትጠየፋለች፡፡ ‹‹አንቺ ምን ታደርጊ… እንዲህ ያሞላቀቅንሽ እኛ ወንዶች ነን… የመቀመጫ አድናቂዎች ሆንን›› እላለሁ፡፡ መቀመጫዋ ሲበዛ እጅግ ግዙፍ ነው፡፡ ባለፈው አንድ የማስታወቂያ ለጣፊ በየቦታው አባዝቶ የለጠፈውን ማስታወቂያ ማንም እንዳልተመለከተው ተረድቶ ምን ማድረግ እንዳለበት ቆሞ ሲያሰላስልና ሄለን ከባጃጅ ስትወርድ አንድ ሆነ፡፡ ባለ ማስታወቂያው ፍዝዝ ብሎ ከተመለከታት በኋላ ወደኔ ዙሮ ‹‹ምናለበት ብከፍላትና ይሄን ማስታወቂያ ከኋላዋ በለጠፍኩት… ሺህ ተመልካች ይኖረው ነበር›› ብሎ አሳቀኝ፡፡
እሷም ቢሆን የወንዶችን ደካማ ጎን ስለምታዉቅ ሁሌም መንገድ ላይ ስትጓዝ የራሷ ብቻ የሆነ የተጠና የአረማመድ ስርዓት አላት፡፡ ግን ምን ያደርጋል ወንዶችን ስታማልል፣ ስትጋበዝ፣ ስትበላና ስትጠጣ ዉላ እንደኔ አይነት ምሰኪን ወንዶችን ታዋርዳለች፡፡ ደሃ ወንድን ስታይ ይጨንቃታል… መንገዱ ይረዝምባታል፡፡ የሚገርመው ደግሞ አባቷ ማታ ማታ አንድ ሆቴል እየጠበቁ፤ በእግር መንገዳቸዉም ባለቤታቸው ቀቅለው የሚሰጧቸውን እንቁላልና ድንች ሲሸጡ ያድራሉ፡፡ አንዳንዴ ‹‹ይቺ ልጅ የአባቷን ድህነትስ እንዴት አምና ልትቀበል ትችላለች?›› የሚል ሃሳብ ይመጣብኛል፡፡
ሎዛ- ደግሞ የምር ቅንነቷ የሚገርም ነው፡፡ ኩንትራት እንድሸኛት ጠርታኝ መንገድ ላይ የተቸገሩ ተሳፋሪዎችን ካየች ‹‹በናትህ አቁምላቸው›› ትለኛለች፡፡ የሷ ሃብቷ የተባበረቻቸውና ያገዘቻቸው ሰዎች ምርቃት ብቻ ነው፡፡ የእሷንና የመሰሎቿን በጎነት ሳስብ ነው የሌሎች ክፋት የሚረሳኝ፡፡ ሳሮንም እንዲሁ ናት፤ በአባቷ ስልጣን የማትመካ፣ በሃብታቸው የማትመጻደቅ፣ ሰውን ሰው ስለሆነ ብቻ ክብር የምትሰጥ… ሩህሩህ… ደግ… የደግነት ጥግ፡፡
****
ባጃጄን በመብራት እና በሰው ሰራሽ ቅጠሎች ያሳመረቻት ሳሮን ናት፡፡ አንድ ቀን ዲኮሬሽን እየሰራን እያለ ‹‹ለምንድን ነው ግን ባጃጄን እንደዚህ የገና ዛፍ ያስመሰልሻት?›› አልኳት፡፡
‹‹ትንሿን ፔንጎ ዉስኪ ሀውስ ባጃጅህ ውስጥ መክፈት እፈልጋለሁ›› አለችኝ፡፡ ሲመሻስ በብዛት ውስኪ የምትጠጣበት ቤት ናት- ፔንጎ፡፡ እና አንዳንዴ ወንዶች ሲደብሯት፣ ፉጋራቸው ሲበዛ… ባጃጃችንን ከውጭ አንድ ጥግ እናቆምና ሙዚቃችንን እስከጥግ ከፍተን እሷ ብላክ ሌብል እኔ ደግሞ ቢጫ ለስላሳ ይዘን እንዝናለን፡፡
‹‹አንተ ጠጣ እንጅ?… ሙዚቃውን ደግሞ ድምፁን ጨምርበት››
‹‹እየጠጣሁ ነው ሳሮኔ! ›› የባጃጄን ቴፕ ድምጽ መጨመሪያ እያሾርኩ… የያዝኩትን የለስላሳ ጠርሙስ እሷ ከያዘችው ብላክ ሌብል ጠርሙስ ጋር አጋጨዋለሁ፡፡ ችርስ! ኪው! ሳሮን ስትጠጣ በብርጭቆ ሳይሆን የጠርሙሱን አንገት አንቃ ወደ ጉሮሮዋ ስታንቆረቁረው ነው ደስ የሚላት፡፡
ወዲያው በመልሴ ፍርስ ብላ ትስቃለች፡፡ ሳቋ እንኳን ካጠገቧ ያለን ሰው ይቅርና በየጉራንጉሩ… በየጫካው… በየሜዳው… በየቤቱ ያለውን ህዝብ በሙሉ የማሳቅ ልዩ ሀይል አለው፡፡
ሳሮን የሳቅ ምንጭ ናት፡፡ ሳቋ ቡል… ቡል… ቡል… እያለ እንደ ምንጭ ሲፈልቅ ሳቅ የደረቀበት እንስራውንና ጀሪካኑን ይዞ በሰልፍ ሳቋን እየጨለፈ የሚስቅ፡፡ በቃ ሳሮን ስትስቅ ሁሉም ሳቋን አብሮ እየተቋደሰ ይመስለኛል፡፡
በቤት ውስጥ ያለው ሃሃሃሃ…
በጭፈራ ቤት ያለ ቂቂቂቂ…
በስራ ቦታ ሃሃሃሃሃ… ጎጡ፣ቀበሌው፣ወረዳው፣ዞኑ፣ክልሉ፣ብሄሮችና ብሄረሰቦች፣በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ሀገሬ እየሳቀች ይመስለኛል፡፡
‹‹ለምንድን ነው ወንዶችን የምትጠያቸው?›› አልኳት በመጠጥ ቤት የምታገኛቸውን ወንዶች በንቀት አይን የምትመለከታቸው ትዝ ብሎኝ፡፡
‹‹አንተ ደግሞ! በጅምላ ወንዶችን የምትጠያቸው ትለኛለህ እንዴ?››
‹‹እንዴት? በጅምላ...›› ወሬዋ ስለሚጣፍጠኝ ተጨማሪ እንድታወራ መንገድ እከፍትላታለሁ፡፡
‹‹…የምጠላው የሚያስጠላኝን ብቻ ነዋ!››
‹‹አሃ!›› ጭንቅላቴን ወደላይና ወደ ታች ነቀነቅሁላት፡፡ አንዳንዴ የተናገረችው ባይገባኝም እንኳን እንደዚህ አደርጋለሁ፡፡ የሆነ ጊዜ በጣም ተመስጣ የሞቀ ወሬ ስታወራኝ ሁለት ሶስት ጊዜ ወሬዋን አቋረጥኳት፡፡ ወዲያው እያወራችኝ ያለው ነገር ግልጽ እንዳለሆነልኝ፤ ይባስ ብሎ እንደተወሳሰበብኝ ስነግራት፡-
‹‹አንተ የሆነ የማገናዘብ ችግር /problem of understanding/ ሳይኖርብህ አይቀርም፤ ሳይካትሪስት ጋ ሄደህ ቼክ ብታደርግ መልካም ነው!›› ብላ መከረችኝ፡፡ ወዲያው ከምክሩ ቀጥላ ‹‹ስማ እንጂ መኪናየን ትቼ ካንተ ጋር በባጃጅ የምዞረው ለምን ይመስልሃል?” አለችኝ፡፡
‹‹እኔ እንጃ!›› ግራና ቀኝ ጭንቅላቴን አወዛወዝኩት፡፡
‹‹…ሰው ስለምወድ ነው! ባጃጅ ውስጥ ስትሳፈር ብዙ ነገር ትታዘባለህ፣ ብዙ ነገር ትማራለህ፣ምንም የማይመስል ባላገር የሚናገረው ቃል በራሱ ምስጢር አለው፡፡ በቃ ቅኔ ነገር ነው፡፡ በኋላ የዚህን ባላገር ቅኔ ለመፍታት አንድ ብርጭቆ ብላክ ሌብል ይዤ እተክዛለሁ፡፡ ተማሪው ራሱ የሆነ ሰምና ወርቅ ነው ንግግሩ፣ ጎዳና የሚያድረውም ልክ እንደዚያው፡፡ እኔ በግል መኪናየ ብሞላቀቅ ይህንን እድል አገኘው ነበር? ኖ! በፍፁም አላገኘውም፡፡ ከሰው ውጭ የሆነ የተገለለ ህይወት ደግሞ ህይወት አይባልም፡፡ በዚች አለም በያንዳንዷ ደቂቃ አዲስ ነገር አለ፡፡ ለምሳሌ አንተ!››
‹‹እ… ‹አንተ› አልሽኝ ልበል?›› በንግግሯ ተመስጬ ስለነበር ‹አንተ› ስትለኝ ደነገጥኩ፡፡
‹‹አዎ!… አንተ ከጥቂት ወራት በፊት በመንገዴም… በህይወቴም…. በእውኔም… በህልሜም እኔ ጋር ያልነበርክ፣ ጭራሽ ከነመፈጠርክም የማላውቅህ ሰው ነበርክ፡፡ ያኔ እንቅስቃሴየ በግል መኪናየ ቢሆን ኑሮ የመገናኘት እድላችን ከዜሮ በታች ነበር፡፡ ድንገት አንተ በባጃጅህ እኔ በመኪናየ የመጋጨት አደጋ ካልገጠመን በስተቀር፡፡
አየህ! በዚያች ቀን ባጃጅ ውስጥ ስሳፈር ካንተ ጋር ተዋወቅሁ፡፡ ሌሎችም አሉ ልክ እንደዚህ በድንገት የተዋወቅኋቸው፡፡ አንድንዶች ሲበዛ ቀልደኞች ናቸው፡፡ የሆነ ነገር ይናገሩና ሳቄን ሳልጨርሰው መጨረሻችን ላይ ደርሰን ወራጅ ሲሉ እናደዳለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አናዳጅ ብቻ ሳይሆኑ አብግኖች ጭምር ናቸው፡፡ ገና በቅጡ ሳንተዋወቅ ‹ስልክ ቁጥርሽን› ይሉኛል፡፡ ለእንደነዚህ አይነቶቹ ደግሞ አባቢ ይሙት ነው የምልህ- ስልክ ቁጥሬን ከምሰጣቸው ስልክ ቀፎየን ብሰጣቸው ይቀለኛል›› ትላለች በእጇ የያዘችዉን ዋጋው ዉድ የሆነ የስልክ ቀፎ እያወዛወዘች፡፡
‹‹…አንዳንዶቹ ደግሞ ጭራሽ የማትተነብያቸው… የማትገምታቸው… የማታጠናቸው… አወቅኋቸው ስትል ምስጢር የሚሆኑብህ የሆኑ አዝግ ነገሮች ናቸው- ልክ እንዳንተ፡፡ የሚገርመው ግን ይሄ ሁሉ ተደማምሮ ነው ለኔ ህይወት ማለት፡፡››
‹‹እኔን አዝግ?›› አልኋት በቀልድ እየተመለከትኳት፡፡
‹‹አዎ! አንተ በጣም አዝግ ነህ! ለምን በለኝ… ከተዋወቅን ስንት ወራት አለፉ፤ ነገር ግን የመጀመሪያ መጠጥህም፣ የመጨረሻ መጠጥህም ለስላሳ ብቻ!››
‹‹ለስላሳኮ ጥሩ ነው… ያነቃቃል!››
‹‹ኧረ በፈጠረህ!... እኔ ለስላሳ መጠጣትም ሆነ ማየት አልፈልግም፡፡ ለስላሳ የያዘ ሰው ካየሁ ስብሰባ ውስጥ ያለሁ ነው የሚመስለኝ፡፡ ስልጠና ላይ ለሻይ እረፍት የወጣሁ፡፡ ቢጫ ለስላሳ ካየሁማ ጭራሽ ይብሰኛል፡፡ የታመምኩ ነው የሚመስለኝ፡፡ የበሽተኛ መጠጥ ነገርኮ ነው፡፡ አንተ ግን ድሮም ለስላሳ አሁንም ለስላሳ! የሆንክ በሽተኛ፡፡››
(ይቀጥላል...)
***
ከ "ሁለቱ ማዶዎች" መፅሃፍ የተቀነጨበ

Mirt article
ReplyDelete