የህልሜ ጓደኛ 3
ከክፍል 2 የቀጠለ....
‹‹ስለአንተ ሁሉን ነገር ነግሬዋለሁ፡፡ ከተዋወቅን ስድስት ወር እንደሆነን… ስንቀሳቀስ ሁሌም የአንተን ባጃጅ እንደምጠቀም… የምፈልገው ቦታ እንደምታደርሰኝና እንደምትመልሰኝ… ከለካፊዎች እንደምትጠብቀኝ… እንደምታዝናናኝ… እንደምታጫዉተኝ… ባጃጅ መንዳት እንደምታለማምደኝ… እና ደግሞ…›› የጀመረችውን ዓረፍተ ነገር ሳትጨርሰው አይኗን እንደጨፈነች ተመስጣ ጥርሷን ብቻ ስታሳየኝ ቆየች፡፡ ከዚያ አይኞቿ ተከፈቱ፡፡
‹‹…እና ደግሞ… እንደ.ም.ወ.ድ.ህ ጭምር!››
በጠራራ ፀሀይ… ወለል ባለ ብርሀን… የሚርመሰመስ ህዝብና መኪና ባለበት መንገድ ዳር… በዚህ ሁሉ መሀል እኔነቴን ማን ዘረፈኝ? ድምፄንስ ምን ዘጋው? ምክንያቱን ሳላውቀው ድጋሚ ጸጥ አልኩ፡፡ ድርቅ እንደ እንጨት! ከኋላየ መጥታ እጇን ጫን ስታደርግብኝ ባለሁበት ቅዠቴ ጀመረኝ፡፡ የተቀደሰ ቅዠት፡፡ ቅዠቱ እንዲህ ሲል ይጀምራል፡-
እኔና ሳሮን ነጭ በነጭ ሙሉ የባህል ልብስ ለብሰን፣ መላዕክቱን መስለን በተቆናጀች ባጃጄ ወደ አባቷ ቤት እንቀርባለን፡፡ አባቷ ነጭ በነጭ የሆነ ሙሉ የባህል ልብስ ለብሰው የቤታቸው ሰገነት ላይ በሩቁ ይታዩናል፡፡ የሆኑ ከየት መጡ ያላልናቸው ሁለት ነጭ መለዮ የለበሱ ሰዎች ሳሮንና እኔን ግራና ቀኝ አጅበው ወደ አባቷ አቀረቡን፡፡ /ያ-ቅዠት የት ሄደ? ያ- የሰይጣኖቹ?/
ሳሮን እሮጣ ሄዳ አባቷን ጥምጥም ብላ ከሳመቻቸው በኋላ ወደኔ እየጠቆመች ‹‹አባየ የነገርኩህ ልጅ ይኼ ነው›› ስትላቸው ከሳሮን በፈጠነ ሮጬ እግራቸው ስር ተደፍቼ ጉልበት ሳምኩ፡፡ ከየት መጣ ያላልኩት ወታደር ከእግራቸው ስር ለአክብሮት የተንበረከክሁትን እኔን በአንድ እጁ አንጠልጥሎ አነሳኝ፡፡ እንደ ሁኔታው እንዳንጠለጠለኝ ሊወረውረኝ ያሰበ ይመስል ነበር፡፡በዚያ መሃል የሳሮን አባት የሆነ ምልክት ሲያሳዩት ወዲያውኑ ቀስ አድርጎ ለቀቀኝ፡፡
የሳሮን አባት ሁለቱንም ሸካራ ጉንጮቼን አገላብጠው ከሳሙኝ በኋላ እሷንና እኔን በግራና በቀኝ እጃቸው ጨብጠውን በጠባቡ የአስፋልት ጎዳና ዉስጥ ለዉስጥ ዛፎቹ በጥላቸው፣ ወፎቹ በዜማቸው፣ ራቅ ያሉት ጠባቂዎች በጠመንጃቸው አጅበዉን ወደ መኖሪያ ቤታቸው ስንገሰግስ ሳሮን በአባቷ ጀርባ በኩል አንገቷን ጠምዝዛ ዝቅ ባለ ድምጽ እንዲህ አለችኝ፡፡
‹‹ስማ ለስላሳ መጠጥ የለንም፤ አንተ መቼም ያለ ለስላሳ አትቀምስም፤ እና ደግሞ እ.ወ.ድ.ሀ.ለ.ሁ››
ይበልጥ ውዥንብሬ ሲወጣ እጄን ያልበኝ ጀመር፡፡ ወደኋላ ዙሬ ስመለከት የአባቷን ጉልበት ስስም እጄን አንጠልጥሎ ያነሳኝ ወታደር ከግቢው በር ላይ ክላሽ ጠበንጃውን እንዳቀፈ ቆሟል፡፡
‹‹እኔ የምለው… በእድሜ የሚበልጡንን ማክበር… ደግ መሪዎቻችንን ማመስገን… እንደ ባህላችን የአባቶቻችንን ጉልበት መሳም የሚከለክል መመሪያ አለ እንዴ?... ማለቴ ጉልበታቸውን በሳምኩ አንገቴን አንጠልጥለህ ያነሳኸኝ?›› ልለው ነበር፤ ወዲያው ግን የሳሮን ድምጽ ቀደመ
‹‹አባየ! ብታየውኮ የሚገርም ልጅ ነው… ያለ ለስላሳ አንዳች መጠጥ ንክች አያደርግም›› አለቻቸው እየተፍለቀለቀች፡፡ በሃፍረት ውስጥ ሆኜ በአባቷ ጀርባ እጄን አሳልፌ ጀርባዋን ቆነጠጥኳት፡፡ እንደ ዉሃ ብይ በሚንቀዋለሉ አይኖቿ ስትጠቅሰኝ እንደገና ድንብርብሬ ወጣ፡፡
‹‹ስማኝማ አባቢ ሚ..ሪንዳ ብቻ ነው የሚጠጣው›› ቂቂቂቂቂቂ… ተናግራ ሳትጨርስ በሳቅ ፍ.ር.ስ እያለች፡፡
‹‹ታዲያ ምን ችግር አለው? ሰው የሚወደውን ነው የሚጠጣው፤ ደግሞ ለስላሳም ቢሆንኮ ከቤት አለ...››
‹‹ኧረ! አባቢ ዛሬማ ‹ብላክ ሌብል› ይጠጣል፡፡ የምር አንድ ብርጭቆ አቀምሰዋለሁ!›› ሳሮን አይኗን እያስለመለመች አባቷን ተከራከረች፡፡ ከዚያም ወደኔ እየተመለከተች፡-
‹‹ሲሳይ! ዛሬ ግን ውስኪ ትጠጣለህ እሺ?››
‹‹እደረግመው!›› ሳላስበው ነው ይሄን ቃል የተናገርኩት፡፡ በንግግሬ ዉስጥ የአመታት የዉስኪ አምሮቴ ቁልጭ ብሎ ይታይ ነበር፡፡
‹‹እ…?›› ክው! አለች ሳሮን፡፡ እንደ ዛሬው ሆና ስትደነግጥ አይቻት አላዉቅም፡፡
‹‹ማ… ማለቴ እጠጣለሁ! በደንብ እጠጣለሁ!›› የእሷ ድንጋጤ ስላስደነገጠኝ ሞኝ በሆነ ድምጽ መለስኩላት፡፡
ለአባቷ ‹‹መጠጥ አይጠጣም›› እያለች ደጋግማ ስትነግራቸው ስለነበርና የኔ ምላሽ ደግሞ ውሸታም ስላስመሰላት በድንጋጤ አንዴ እኔን አንዴ አባቷን በፈረቃ ትመለከተን ጀመር፡፡
‹‹…የማልጠጣው ድህነት አቆራምዶኝ እንጂ ውስኪ ጠልቼ ይመስልሻል? በርግጥም ለስላሳ ከመጠጣት ተሻግረን፣ ቮድካና ብላክ፣ ቁርጥና ጥብስ የምናማርጥበት ገንዘብ እንደ ቁምጣ ቢያጥረን እንጂ፣ በርግጥም አንቺ ስትለይኝ ሱሴን ማን ያስታግስልኛል? ብየ ፈርቼ እንጂ… መጠጥ ጠልቼ ይመስልሻል?
የማንናገረው… ሰሚ አጥተን፣
የማንጠጣው… ድህነት ቅኝ ገዝቶን፣
የማንዘንጠዉ… ኑሮ እያንገላታን፣ መላዉ ቢጠፋብን እንጅ ከለስላሳ ጋር የትኛው ፍቅር ይዞን ነው? አላወቅሽኝም ሳሮን…›› አልኩኝ በውስጤ፡፡
ባለፈው የነገረችኝ ነገር በጭንቅላቴ መጣ ‹‹ባላገሩ የሚናገረው፣ ተማሪዉ፣ ጎዳና አዳሪው የሚያወራዉ ሁሉ በራሱ ቅኔ ነገር ነው… እሱን ለመፍታት አንድ ጠርሙስ ብላክ ሌብል ይዤ እተክዛለሁ›› ያለችኝ፡፡ ‹‹…ሳሮኔ እኔምኮ የኑሮ ዉድነት ያስመረረኝ፣ ድህነት ሰቅዞ ያሰረኝ ቅኔ ነገር ነኝ፤ ዛሬ ፍችኝ› ወለል ባለው አስፋልት ከራሴ ጋር እየተነጋገርኩ ቤታቸው እስከምንደርስ ናፈቀኝ፡፡
‹‹ኧረ ውስኪ ናልኝማ… ቺርስ! ከሳሮን ጋር… ቺርስ! ከአባቷ ጋር…
ከሃብታምና ከሩህሩህ ባለስልጣን ልጅ ጋር ተፋቅሮ፣ ሳሮንን የመሰለች ፍልቅልቅ… ቅን… ሃብትና ስልጣንን ተገን አድርጋ ድንበር የማትከልል… ድህነቴን አምና የነገ የመለዉጥ ተስፋየን የተለመች ሴት ጋር ሆኜ እንዴት ለስላሳ ልጠጣ? አጋፋሪ ናወዲህ ውስኪ ቅዳልኝማ...ቺርስ!!!
(አለቀ)
ከሁለቱ ማዶዎች መፅሀፍ የተወሰደ

Comments
Post a Comment