ገረዲቱ - ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት

ገረዲቱ
እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በጎም ሆነ ደግ ታሪክ ሳይስተናገድበት አያልፍም፤ በሥነ ፍጥረት ታሪክ ውስጥ ብትመለከቱ ምንም ሳይሠራ ያለፈ ሰው ታገኙ ይሆናል እንጅ ምንም ሥራ ያልተሠራበት ቀን አታገኙም፤ ምክንያቱም ጊዜ የተፈጠረው ለሥራ ነውና:: ከመጀመሪያዋ ጊዜ ጀምሮ እግዚአብሔር ያላ ሥራ ያሳለፋት ጊዜ አትገኝም፡፡ በእያንዳንዳችንም ሕወት ውስጥ እለታት የየራሳቸው የሆነ ልዩ ልዩ ታሪክ አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ የወደቅንባቸው አንዳንዶቹ የተነሣንባቸው፣ የተደሰትንባቸውና ያለቀስንባቸው፣ እግዚአብሔርን  ያገኘንባቸው ወይም ከሰይጣን ጋር ማኅበርተኛ የሆንባቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ 
ለዛሬው እንኳን ይህን የምላችሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፊ ታሪክ ስለተመዘገበለት አንድ ቅዱስ ሰው ልነግራችሁ ፈልጌ ነው፤ ሰውየው ገሊላዊ፣ ትውልዱና ነገዱ ዕብራዊ ሲሆን ያደገው በታላቁ የገሊላ ባሕር አጠገብ ነው ዋና ሥራው አሣ አጥማጅነት ሲሆን የቀደመ ስሙ ስምዖን ወልደ ዮና የክርስትና ስሙ ደግሞ ጴጥሮስ ይባላል፡፡ ይህ ሰው እግዚአብሔር በእርጅና ዘመኑ የባረከው ሰው ነው፤ መቸም እግዚአብሔር ለእያንዳንደችን ያዘጋጃት የመጎብኘት ቀን እንዳለች እናምናለን፣ ከዚህም የተነሣ አንዳንዶችን  በማሕጸን ሳሉ እንደነ ኤርምያስና ዮሐንስ መጥምቅ ያሉትን፣አንዳንዶችን በጨቅላነት እድሜ እንደነ ቅዱስ ቂርቆስ፣ አንዳንዶችን በወጣትነት እንደነ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊና እንደነ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያሉትን አንዳንዶችን በእርጅና ዘመናቸው እንደነ ቅዱስ ጴጥሮስ ያሉትን ጎብኝቷቸዋል ፡፡ ከሰው የሚጠበቅ የሚጎበኝበትን ቀን ደጅ መጥናት ነው እንጅ ሌላው የእግዚአብሔር ድርሻ ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስም እግዚአብሔር የወሰነለት ቀን ስትደርስ በትጋት ሆኖ ከሚሠራበት ቦታ ሂዶ ጎበኘው፣ ለቤተ ሰብነት አጨው፡፡ በዚህ ምክንያት ከራሱ አልፎ ቤተ ሰቦቹንም በእግዚአብሔር በረከት እንዲጎበኙ ያደረገበት ጊዜ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እውነት ነው ማቴ      ተባርኮ ቤተ ሰብን ማስባረክ እንዴት መታደል ነው፤ ኢየሉጣነ ለሰማዕትነት ያበቃት የቂርቆስ ጽናት እንደሆነ ታውቃላችሁ? የህጻኑን ጸሎት የሰማው አምላክ እናቱን አጸናለት የጴጥሮስንም ጭንቀት ተመልክቶ ቤቱ ድረስ ሂዶ አማቱን ከንዳዷ ፈወሰለት፤ ድሮ አሣ እያጠመደ ከሚረዳቸው መርዳት ይልቅ አሁን ከእግዚአብሔር ጋር ሲሆን የረዳቸው መርዳት በለጠ፡፡ 
ዳሩ ግን ምን ይሆናል ሰው በሕይወቱ ሁል ጊዜ ስኬታማ መሆን እንደምን ይሆንለታል፤ ከእለታት አንዷ የቅዱስ ጴጥሮስ እምነት በፈተና የሚረጋገጥባት ቀን ነበረችና "ሰዎች እኔን ማን ይሉኛል?" የሚለውን ጥያቄ በመምህሩ ተፈትኖ በታላቅ መዐርግ በመጨረሱ መልካም ውጤት ያስመዘገበው ጴጥሮስ እንደ ቀድሞው በመምህሩ ሳይሆን ሌላ ፈታኝ ከፊቱ ቆሞ እየፈተነው ነው፡፡ የሊቀ ካህናቱ ገረድ ናት፡፡ ፈተናው አንተ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ነህ የሚል ነው፤ እውነት ለመናገር የትኛው ይከብዳል? የክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት ከማወቅና የእርሱ ደቀ መዝሙር ነኝ ብሎ ከመናገር፤ የክርስቶስ አምላክነት እኮ ከአዋቂዎች ሳይቀር የተሰወረ ጥበብ ነው፡፡ ይህን መመለስ የቻለው ጴጥሮስ ዛሬ ግን በትንሽ ፈተና ውጤቱ ሲያሽቆለቁል  እናየዋለን፤ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? የመጀመሪያውን በትክክል የመለሰው ከክርስቶስ ጋር ስለነበር ነው ሁለተኛው ግን ብዙ ችግር ነበረበት፡፡
ጴጥሮስ እንደ እግዚአብሔር ቃል መሔድን እንቢ ብሎ በትዕቢት እየተጓዘ የነበረበትና ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ሁሉን ማድረግ ይቻላል ብሎ እየተጓዘ የነበረበት ጊዜ ስለነበር ምንም ሳይመልስ ቀረ፡፡ ሰው ያለ ፈቃደ እግዚአብሔር ምን ማድረግ ይችላል? ጴጥሮስ ይህን ሳያውቅ ክርስቶስ ስለእርሱ የተናገረውን አልቀበልም አለ፡፡ ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ትክደኛለህ ቢባል እኔ አላደርገውም ብሎ የመምህሩን ሃሳብ ተቃወመ፡፡ እንዲያውም እነዚህ ሁሉም ቢክዱህ እኔ አልክድህም በማለቱ በወንድሞቹ ለይ ሳይቀር ተሳለቀባቸው፡፡ እንዲወድቅ ምክንያት የሆነው ይህ ትምክህቱ ነው እንጅ ሌላ ምንድነው?
በዚህ ዓለም ስትኖሩ እግዚአብሔር ካልደገፋችሁ ከትልቁ ይልቅ በትንሹ፣ ከጠበቃችሁት ይለቅ ባልጠበቃችሁት ጠላት እንደምትሸነፉ በእውነት እነግራችኋለሁ! የእግዚአብሔር መግቦት ባይጠብቀን ኖሮ ትንኝን እንኳን መቋቋም የማንችል መሆናችንን ታውቃላችሁ? የወባ ትንኝ ስትተነፍስበት የሚዝለፈለፍ ሰውነት ነው እኮ የያዝነው፡፡ እንዲየውም በዚህ ምድር ላይ ዝሆኖች ከሚያበላሹት ይልቅ ዝንቦች ያገሙት ነገር ይበዛል፡፡ 
አስተውሉ! ሁሉ በእርሱ ሆነ ተብሎ ተጽፏል ዮሐ 1÷3 ያለ እርሱ ምንም ማድረግ እንደማንችልም አስጠንቆናል ዮሐ 14፡፡ ከዚህ መመሪያ በወጣን ቁጥር በጥቂቱ ለጠላት ተላልፈን እንሰጣለን፤ እንደዚያማ ባይሆን ኖሮ ጴጥሮስን ገረዲቱ እንደምን ታሸንፈው ነበር፤ እስኪ ልብ በሉና ተመልከቱ ጌታችን በተያዘባት ሌሊት ሁሉም ደቀ መዛሙርት ዝምሲሉ ሰይፍ መምዘዝ የቻለ ብቸኛው ጀግናኮ እሱ ነበር፡፡ ሁለት መቶ ወታደር ከፊቱ ሰይፍና ጎመድ ይዞ ተሰልፎ እሞታለሁ ብሎ ሳይፈራ በመዘዘው ሰይፍ  ሊቀ ካሕናቱን ባሪያ ጆሮውን ቆርጦ እንዳልጣለ ዛሬ በአንድ ገረድ ፊት መመስከር ሳይችል እንደምን ቀረ ትላላችሁ? አላልኋችሁም!  የጴጠሮስ ጉልበቱ ከፈጣሪው ጋር መኖሩ ነው፡፡
ከእግዚአብሔር ጋር ኑሩ ትጸናላችሁ እንኳን እንዲህ እንደትንኝ በሆነ ኃይል ቀርቶ ተራራ ማፍለስ የሚችል ጉልበት የሚገኘው ከእርሱ ጋር ለሚኖሩት እንደሆነ ሳልጠራጠር እነግራችኋለሁ፤ ‹‹የተራራ ያክል ሃይማኖት ቢኖራችሁ ይህንም ተራራ ከዚህ ተነቅለህ ሂድ ብትሉት ይሆንላችኋል›› እንዲል ማቴ 17    ለእግዚአብሔር መታዘዝ ጉልበት እንደሆነ ተመልከቱ ከጉብዝና ወራት ይልቅ በእርጅና ዘመን ጉልበታም ያደርጋል፤ ምክንያቱም እሺ ብለው ለሚታዘዙ ሰዎች እሺ ብሎ ማንኛውንም ሥራ የሚሠራላቸወ እግዚአብሔር እንደሆነ በእምነት ስለምናውቅ ነው፡፡ 
እሺ ባለማለታችን ስንት ቀን ከገረዲቱ ጥያቄ የተነሣ  ሳንፈልግ ያሰብነውን ሳይሆን ያላሰብነውን፣ የምናምንበትን ሳይሆን የማናምንበትን ተናግረናል፡፡ መሆን የማንፈልገውን የሆንበት፣ መኖር ከማንፈልገው ሥፍራ የኖርንብት ጊዜ እጅግ በጣም ብዙ ነው፡፡ ገረዲቱ ከክርስቶስ ለተለዩ ሰዎች አስቸጋሪ ናት፤ አዘውትራ ክርስቶስን እንዳንከተል ወደ ኋላ ትስባለች፤ በልባቸው የሚመኙትን እሳቱን እያነደደች፣ እሳቱን ጥለው ክርስቶስን ተከትለው እንዳይሄዱ ደግሞ ውርጯን እንደ በረዶ እያወረደች፣ ሲያስፈልግም በጥያቄ ወጥራ ወደ ክርስቶስ እንዳይመለከቱ በመካከል እየገባች በወሬ አውራ ይዛ ወደ መስቀሉ እንዳይመለከቱ ማድረግ ነው ዓላማዋ፡፡ 
ይህን መልዕክት የምታነቡ ሁላችሁ! በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ገረዲቱ  ልኳችሁ ዓለምን ነው፤ ስንቱን ሰው ከክርስቶስ ጀርባ ወደ ኋላ እንዲመለስ አድርጋዋለች መሰላችሁ፤ በእናንተስ ሕይወት ውስጥ ጥያቄዋ ቦታ ያገኘ ይመስላችኋል? በእናንተና በቤተ ክርስቲያን መካከል ገረዲቱ ካለች ትኩረታችሁ ለሷ ምን እመልሳለሁ እንጅ የቆማችሁለት የመስቀሉ ነገር አይሆንላችሁም ትዝ አይላችሁም? ጴጥሮስም እኮ ወደ ሊቀ ካህናቱ ግቢ የዘለቀው የክርስቶስ ጉዳይ አሳስቦት ነው፤ በእውነት ወንድሞቹ ሁሉ ከአትክልቱ ሥፍራ በር ላይ ጌታ ሲያዝ እንዳዩ ተበትነዋል መጨረሻውን ለማየት የተከተለ ከእነርሱ አንድም የለም፤ ጴጥሮስ ግን የገረዲቱ ነገር አስመለሰው እንጅ ጉዞ ጀምሮ ነበር፡፡
ከእኛ ጓደኞችም እኮ ጫቱ፣ ሲጋራዉ፣ መናፍቅነቱ፣ ዝሙቱ፣ ሆዳምነቱ፣ ፖለቲካው፣ ዘፈን ጭፈራው፣ ስንቱን እነግራችኋለሁ? እነዚህ ሁሉ ገና ከበር ሲያስቀሩዋቸው አንተ ግን እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ተከትለህ ገብተህ ይሆናል እውነት እልሃሁ! ገረዲቱ እየተከተለች ጥያቄ ማቅረቧ ስለማይቀር ተጠንቀቅ፤ አንተኮ በልብህ እያሰብህ ያለኸው ለሞትም ለእስራትም ቢሆን ክርስቶስ በሄደበት ሁሉ እንደምትሄድ ነው አይደል? ግን ይሄን በገረዲቱ ፊት በድፍረት መናገር ትችላለህ? የምታቀርብልህን የዘረኝነት፣ የዝሙት፣ የትዕቢት ጥያቄ ንቀህ፣ አሸንፈህ ማለፍ ትችላለህ? 
እንዲህ እንድትችል ደግሞ አንድ ጥበብ ልንገርህ፤ ቅዱስ ጴጥሮስ በመጨረሻው ቀን ክርስቶስ ለጠየቀው ጥያቄ ሲመልስ ‹‹እንደምወድህ አንተ ታውቃለህ›› ዮሐ 21÷16 የሚል መልስ ሰጥቷል ትክክለኛው የክርስትና መልስ ይህ ነው፡፡ አንተም እንዲህ ልትል ይገባሃል፡፡ እሱን መውደድ አለመውደዳችንን ከእኛ ይልቅ እርሱ ያውቀዋልና ነው፡፡ እንዲህ ብትል ክርስቶስ ለሌላ ሀላፊነት እንደሚሾምህ ሳልጠራጠር ነው የምነግርህ፡፡ ጴጥሮስን የቤተ ክርስቲያን ጠባቂ አድርጎ የሞተለትን ደሙን ያፈሰሰለትን መንጋ ባለ አደራ ያደረገው ከዚህ በኋላ ነውና፡፡  
ከዚህ ሀሉ ነገር በጣም የሚገርመው ነገር ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? በገረዲቱ ጥያቄ ማለፍ አልችል ብሎ አፍሮ ወደ ኋላ የቀረውን ጴጥሮስን ፍለጋ የክርስቶስ ዐይኖች ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ዘወር ብለው ይመለከቱ ነበር ሉቃ 22     የበደላችሁት ሰው እናንተን ለማየት ፈቃደኛ ነውን? ሐጢአትም እንኳን ብናደርግ ዐይኖቹ እኛን ከመፈለግ ወደ ኋላ አይሉም፤ ሃይማኖትን ከመካድ በላይ ከባድ ሐጢአት የለም በጴጥሮስ ሕይወት የተከሠተው ችግር ደግሞ ይህ ነው፡፡ 

ትንሿን በደላቸውን እግዚአብሔር ይቅር እንደማይላቸው በማሰብ አፍረው የቀሩትን ከቤቱ የጠፉትን  ንገሯቸው፤ ያለ ሐጢአት ከመያገለግሉት አገልጋዮቹ ይልቅ ባንተ በሐጢአተኛው ይደሰታል በሉት፤ እንዲያውም እኮ ጴጥሮስ ሳይክድ ገና ጌታችን ዞሮ እሱን እንደተመለከተው አልተጻፈም ዶሮ ሳይጮህ ሦስት ጊዜ ሲክ ድ ገረዲቱን መሸነፍ አልችል ሲል ዘወር ብሎ ተመለከተው፤ እርዳታ የሚያስፈልገው ለወደቀ ሰው አይደል!
/በሊቀ ሊቃውንት ስምዓ ኮነ መልአክ/

Comments

Popular posts from this blog

የህልሜ ጓደኛ 3

የህልሜ ጓደኛ 2