የከሸፈ ትውልድ 1
ክፍል 1 - Part 1
ጥሎብኝ በተለያዩ ምክንያቶች ራቅ ወዳሉ ቦታዎች በህዝብ ትራንስፖርት ስንቀሳቀስ ሴቶች ጋር ብቀመጥ እመርጣለሁ፡፡ በተቻለኝ አቅምም ሴቶች ጋር ለመቀመጥ አመቻቻለሁ፡፡ ‹‹የሆነ የሴት ዛር ሳይለክፍህ አይቀርምኮ…›› ይሉኛል ጓደኞቼ፡፡ እኔ ግን አሁንም እደግመዋለሁ! ምርጫዎቼ ሴቶች ናቸው፡፡ ወዳጄ ያለ ሴቶች መንገዱ ብቻ ሳይሆን ህይወትም ባዶ ትመስለኛለች፡፡
ከስንት አመት በፊት ያኔ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እያለን በጾታ እኩልነት/ጀንደር/ ዙሪያ ስንወያይ ከመካከላችን ፍልስፍናውን እዉቅና የሰጠንለት አንድ ተማሪ እንዲህ ሲል ተከራከረ፡፡ ‹‹female is unfinished creature. ሴቶች ዉጥን ፍጡሮች ናቸው! ገባህ አንድ አካል ሙሉ እንዲሆን ከሚሰራበት ቁስ /elemenet/ ከእያንዳንዱ የሚያስፈልገዉን ያህል መጠን ወስደህ መገጣጠም ይኖርብሃል፡፡ ለምሳሌ ዉሃን እንመልከት! ዉሃ ዉሃ እንዲሆን /በፕላስቲክ ጠርሙስ የያዘዉን የታሸገ ዉሃ ከፍ አድርጎ እያሳየን/ ሁለት እጅ ሃይድሮጅንና አንድ እጅ ኦክስጅን ነው የምንጠቀመው፡፡ መጠኑ ከዚህ ከፍ ወይም ዝቅ ቢል ግን በፍጹም ዉሃን አትሰራዉም፡፡
አየህ!… ሴት ግን ከዚህ በታች ናት፡፡ ለምን? የሚል ጥያቄ ልትጠይቅ ትችላለህ፡፡ ምክንያቱም አዳም ከተሰራበት ነገር አንድ በአንድ መካፈል ነበረባት፡፡ ከደሙ ደም፣ ከስጋው ስጋ፣ ከአጥንቱ አጥንት ስትወስድ ነው ሙሉ ሰው የምትባለው፡፡ እሷ ግን ከቁራጭ አጥንት ብቻ ነው የተሰራችው!›› ሲል ተከራከረ፡፡ መከራከር ብቻም ሳይሆን ምንጩ እዉነት መሆኑን እስካሁን ባናረጋግጥም እሱ ግን እዉቁ ፈላስፋ ኒቼ እንደተናገረው በልበ ሙሉነት ነገረን፡፡ እንዲህ ሲፈላሰፍብን ሁላችንም ከልባችን ነበር የምናዳምጠው፡፡
በዚያች ቅጽበት ለብቻው መድረኩን ተቆጣጥሮት የነበረው ልጅ ሁለት ደጋፊዎችን ለማፍራት ቻለ፡፡ ‹‹ልክ ነው›› የሚሉ ሁለት ጨበሬ ወጣቶች ከጎኑ ተሰለፉ፡፡ ይባስ ብሎ አዲስ የተቀላቀለው አንደኛው ወጣት ሴትን ዝቅ የሚያደርግ ተጨማሪ የፍልስፍና ንግግር አከለ ‹‹ሴቶች የእድገት እንቅፋቶች ናቸው- females are an obstacle for development! ›› ሲል ደመደመ፡፡ ሃሳቡን የሚደግፉት በአሸናፊነት መንፈስ ደረታቸውን ነፍተው ተቃራኒ ሃሳብ የሚያነሳ ሌላ ወገን ካለም የማያዳግም የመልስ ምት ለመስጠት ከፊት እስከ ኋላ የተቀመጥነውን በሙሉ በአይናቸው ሲያማትሩ ሌሎች ደግሞ በልጁ አነጋገር እየተሳሳቁ መቀላለድ ጀመሩ፡፡
ከክርክሩ መሃል የነበሩት ሴቶች በንዴትና በተሸናፊነት መንፈስ እርር ድብን እንዳሉ በዚያ ቅጽበት ወደ ክፍላችን መምህር እየገሰገሰ ስንመለከት ተሯሩጠን ወደ ክፍል ገባን፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች መሰል የጾታ ክርክሮችና ዉይይቶች ሲነሱ ይበልጥ ክርክሩ እንዲጧጧፍ እነዚያን ጥቅሶች ምንጭ ጠቅሼ እናገራቸዋለሁ
‹‹ሴቶች የእድገት እንቅፋቶች ናቸው!››
‹‹ሴቶች ዉጥን ፍጡሮች ናቸው!›› የሚሉትን፡፡
በአንድ ወቅት ደግሞ ከፌስቡክ የመረጃ መረብ ላይ አንዲት ደስ የምትልና ቀደም ብየ የጠቀስኳቸውን ሁለት ፍልስፍናዎች የምታጣጥል ቀልድ ብጤ ነገር አነበብኩ፡፡ በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ ዓመተ ምህረት አጋማሽ አካባቢ ነው፡፡ ያኔ ሳር ቅጠሉ ሁሉ ‹‹አብዮቱ ይለምልም!›› የሚል ጽሁፍ የሚጻፍበት፣ጋዜጣና መጽሄቱ፣ ሬዲዮና ቴሌቪዥኑ ሁሉ አብዮቱን ሲያሞካሽ ዉሎ የሚያድርበት ጊዜ ነበር፡፡ ታዲያ በአንድ አብዮታዊ ሰልፍ ላይ በአንድ እጁ ድምጽ ማጉያ በሌላኛው እጁ ደግሞ ስፍር ቁጥር የሌላቸው አብዮታዊ መፈክሮች የተጻፉበት ወረቀት የያዘ ግለሰብ አይኖቹን ወደ ወረቀቱ ከላከ በኋላ አንደኛዉን መፈክር በሚዝገመገም ድምጹ አነበበው፡፡
‹‹አብዮቱ ያለ ሴቶች ተሳትፎ ግቡን አይመታም!››
ከሰልፉ መሃል የነበረ ሌላ አብዮታዊ ተሰላፊም ‹‹ልክ ነህ! ያለ ሴቶች ተሳትፎ እንኳን አብዮቱ ግቡን ሊመታ ቀርቶ ሌሊቱም አይነጋም!›› አለ አሉ፡፡
አየህ! ከሴቶች ጋር ስትሆን ይች አለም ከነሙሉ ገመናዋ ዉልል ብላ ትገለጥልሃለች፡፡ ሴትነት ዉስብስብነት ነው… እነሱ በዉስጣቸው የያዙት መጥፎም ሆነ ጥሩ ገጠመኞቻቸው ከእኛ ከወንዶች በእጥፍ ይበልጣል፡፡ አለፍ ብለህ ካሰብህ ደግሞ ከእነሱ የምትማረው የህይወት ገጠመኝ እጅግ ብዙ ነው፡፡ ለዚያ ነው ሴቶችን ሴቶችን የሚያሰኘኝ፡፡
ረጅም የመኪና ጉዞ ላይ ከአጠገቤ ወንበር ከተጋራኝ በኋላ እንቅልፉን ከሚለሸልሽ አሊያም ደግሞ ሞባይል ስልኩ ላይ አፍጥጦ መዉረጃው ቦታው ላይ ሲደርስ ከሚባንን ገልቱ ወንድ ጋር ተቀምጬ ጉዞየን ማበላሸት አልፈልግም፡፡ እድል ካልጣለኝ በስተቀር፡፡
ሴቶች ግን ከነገርኩህ በላይ ናቸው፡፡ ፊታቸው ተቋጥሮ… ከንፈራቸው ተከድኖ ቢሆን እንኳን ሺህ ጊዜ ከወንዶች ይሻላሉ፡፡ ለዚያ ነው ከእነሱ ጋር መሆን የሚያስደስተኝ፡፡ ይኸው ዛሬ ግን ቀን ጣለኝና ከወንድ ጋር አንድ ወንበር ተጋርቼ ተቀመጥሁ፡፡ ያዉም አዉቶቡስ ዉስጥ፡፡ ****
በጠዋት ተነስቼ ወደ አዉቶቡስ መናኸሪያ ገሰገስኩ፡፡ ከመኪና ረዳቶች ‹‹የት ነህ?›› ጥያቄና ጉተታ በጥቂቱም ቢሆን ለማምለጥ ሮጥ ሮጥ እያልኩ በዚያዉም መኪኖቹ ከፊት ለፊታቸው የለጠፉትን የጉዟቸው መዳረሻ ታፔላ እየተመለከትሁ ነበር፡፡ ወዲያው በተለምዶ ኮስትር ተብሎ በሚጠራው መለስተኛ አዉቶቡስ ፈጥኜ ገባሁ፡፡ ከፊት አካባቢ ያሉት መቀመጫዎች ስለተያዙ ከኋላ ላይ ወዳሉት ወንበሮች እየገሰገስኩ በዚያዉም እያጫወተችኝና ፈገግታዋን እየመገበች የምታደርሰኝ ቆንጆ ሴት እያማተርሁ ነበር፡፡ ያሰብኩት ሳይሳካ ቀረና ከኋላ አካባቢ ያለ ነጻ ወንበር ላይ ለብቻየ ተቀመጥኩ፡፡
የተቀመጥኩበት ወንበር የመኪናው ጎማ ያለበት አካባቢ ስለሆነ ምቾት እንደማይሰማኝ በማሰብ ክፍት ወንበር ማማተር ጀመርኩ፡፡ ያን ቀን እድለኛ አልነበርኩም፡፡ አማራጭ ሳጣ ከመሀል አካባቢ ካለ ወንበር ላይ አንድ እድሜው በስልሳዎቹ የሚገመት ሰው ለብቻው ተቀምጦ ስላየሁ እሱ ጋር ለመቀመጥ ወሰንሁ፡፡
ጉዞአችን እጅግ እረጅም ባይሆንም አጭር የሚባልም አልነበረም፡፡ ከባህር ዳር አዉቶቡስ መናኸሪያ ተነስተን ሁለት መቶ ስልሳ ኪሎሜትር ገደማ ከምትርቀው ደብረ ማርቆስ ከተማ ነበር ማረፊያችን፡፡ መኪናችን እየገሰገሰ ፍኖተ ሰላም ከተማን ስናቆራርጥ ዉስጤን የርሃብ ስሜት ስለተሰማኝ ትንሽየ የጉዞ ቦርሳየ ዉስጥ የያዝኩትን ብስኩትና የላስቲክ ዉሃ አዉጥቼ እያዋሃድኩ መብላት ጀመርኩ፡፡
ከሰውየው ጋር አንድ ወንበር ተቀምጠን ይሄን ያህል ኪሎሜትር ስንጓዝ አንዳች ነገር አልተነጋገርንም ነበር፡፡ የሆነ የተጠረዘ የጥናት ወረቀት የሚመስል ነገር አስር ጊዜ ያገላብጣል፡፡ እኔ ደግሞ ስልኬ ላይ ፌስቡክ እየተመለከትኩ ነው ፍኖተሰላም የደረስነው፡፡ ድሮም ወንዶች ጋር መቀመጥ ይሄ ነው ትርፉ ድብርታሞች! አልኩኝ በዉስጤ፡፡ ወዲያው የወዳጄ ልዑል ስር የሰደደ የወንዶች ጥላቻና ለሴቶች የሚያደርገው እንክብካቤ ትዝ ብሎኝ ብቻየን ልስቅ ሲቃጣኝ ወደ መሬት አቀርቅሬ ‹‹ቱፍ›› ብየ አለፈልኝ፡፡
ልኡል ካፌ ገብቶ ወንድ አስተናጋጅ ሊያስተናግደው ከመጣ በድፍረት ‹‹ባክህ ሴት አስተናጋጅ ጥራልኝ!›› ይላል፡፡ እኛ አብረነው ከሆንን ድንጋጤያችንን ሸፍነን እንሳሳቅና ነገሩን ቀልድ እናስመስለዋለን፡፡
አንድ የሆነ ቀን ባህር ዳር ዉስጥ አሉ ከሚባሉት ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ዉስጥ ማኪያቶ ለመጠጣት ተሰባስበን ገባን፡፡ ከፊት ለፊታችን ሶስት የሚሆኑ የወንድ አስተናጋጆች ተመሳሳይ ልብስ /ዩኒፎርም/ ለብሰው በክብር ቆመው የተስተናጋጅ ትዕዛዝ ይጠባበቃሉ፡፡ የተወሰኑት አስተናጋጆች ደግሞ ወዲያ ወዲህ እያሉ ተገልጋዮችን ያስተናግዳሉ፡፡ የሚገርመው ደግሞ አስተናጋጆቹ ብቻ ሳይሆኑ ሆቴሉ ዉስጥ የነበሩት ተስተናጋጆችም አብዛኞቹ ወንዶች ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ ሆቴሉ ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ ይመስላል፡፡
ልኡል በራፉን አልፎ ሁለት ያህል እርምጃዎችን ወደ ዉስጥ ከተራመደ በኋላ የሆቴሉን አራቱንም ማዕዘን በሙሉ በአይኑ ቃኘው፡፡ ጠረጴዛ ከበው ወንዶች ብቻ ያዉካካሉ፡፡ በንዴት ጡፎ ወንበር ላይ እስከምንቀመጥ ሲጠብቀን የነበረውን አስተናጋጅ ምልክት አሳየው፡፡
‹‹አቤት ጌታየ ምን ልታዘዝ?››
‹‹ስማ እዚህ ቤት ሰው የለም?›› ሲል ጠየቀው፡፡
አስተናጋጆችና ተስተናጋጆች ግራ ተጋብተው ወደ ልዑል አፈጠጡ፡፡ ልዑል የተናደደ ፊቱን ጨፍግጎ ወደ ዉጭ ሲገሰግስ እኛ ደግሞ ሳቃችንን በእጃችን አፍነን ከሆቴሉ በፍጥነት ወጣን፡፡ በቃ! ልዑል ሴት የምትባል ነገር እስከሌለች ድረስ ሺህ ወንድ በፊቱ ቢተራመስ ሰው ያለ አይመስለውም፡፡ ለዚያ ነው ‹‹እዚህ ቤት ሰው የለም?›› ብሎ የሚጠይቀው፡፡ በእሱ አስተሳሰብ ከመቶ ወንዶች ይልቅ አንዲት እንስት እንደ ሰው ትቆጠራለች፡፡ አበቃ!
****
መኪናችን መክነፉን ቀጥሏል፡፡ የያዝኩትን ደረቅ ብስኩት በዉሃ እያራስኩ አላምጣለሁ፡፡ ወንበር የተጋራኝ ተሳፋሪ ደግሞ ያንን ጥራዝ ማገላበጡን ቀጥሏል፡፡ ዝምታችንን ለመስበር ፈልጌ የያዝኩትን ደረቅ ብስኩት እያስጠጋሁለት ‹‹እንብላ›› አልኩት፡፡
‹‹አመሰግናለሁ…ይቅርብኝ›› አለኝ፡፡ እኔም እንብላ ያልኩት ለይስሙላ እንዳልሆነ ለማሳወቅ ‹‹ችግር የለዉም አንድ ፍሬ ያዝ›› አልኩት ይበልጥ ብስኩቱን እያስጠጋሁለት፡፡
‹‹…አይ! ስኳሯን ስለፈራኋት ነው፤ ይቅርብኝ፡፡ ለግብዣህ ግን ድጋሜ አመሰግናለሁ›› አለኝ፡፡ ‹‹ስኳሯን ስለፈራኋት ነው›› ያለኝ ብስኩቱ ውስጥ የተጨመረው ጣፋጭ ነገር ለጤናው ጥሩ እንዳልሆነ ሲነግረኝ ነው፡፡
ከዚያች ‹‹የእንብላ- አልበላም›› ንግግር ከተነጋገርንባት ጊዜ በኋላ ጨዋታችን ቻይና እንደሰራችው የወፍጮ ሞተር እየጋለ ሄደ፡፡ ሰዉየዉን ጥያቄ የምጠይቀዉም ሆነ ወዲያው ደግሞ ለጥያቄው የግምት መልስ የምሰጠው እኔ ብቻ ሆንኩ፡፡ እሱ ግን ሲናገርም ሆነ የምናገረውን ሲያዳምጥ ቀስ ብሎ ነው፡፡ ለአንዳንድ ጥያቄዎች መልስ ሲመልስም በእርጋታ ነው፡፡ ደግሞ የመልሱ ጥልቀት ይገርመኛል፡፡ ትንታኔው ቀስስስ እያለ እንደ ወራጅ ዉሃ ይፈሳል፡፡
‹‹ስምህን ግን አላስተዋወቅኸኝም?›› አለኝ ሰውየው፡፡ ሙሉ ስሜን ነገርኩት፡፡ ቀጥየም የተወለድኩበትን ሰፈር… የተማርኩበትን ትምህር ቤት ሳይቀር ያለ ማንም አስገዳጅነት በራሴ መልካም ፍቃድ ዘርግፌ ከነገርኩት በኋላ ለመስክ ስራ ወደ ደብረ ማርቆስ ከተማ እየሄድኩ እንደሆነ አከልሁለት፡፡
ጨዋታ ከጀመርን በኋላ የሚናገራቸውን ነገሮች በመመርመር የራሴን ግምት ለማስቀመጥ ሞከርሁ፡፡ ምርመራየ ሰዉየው ምን አይነት ሰው እንደሆነ ለማወቅ መሆኑ ነበር፡፡ ነገር ግን ስለ ሰዉየው አጥጋቢ ግምት መገመት ስላልቻልኩ ቀጣይ ጨዋታችን እንዳይቋረጥ በማሰብ በወሬ ላይ ወሬ፤ በጥያቄ ላይ ጥያቄ እየሰነዘርኩ የሰውየውን ምላሽ ማዳመጥ ቀጠልኩ፡፡
ወደ መዳረሻችን ደብረ ማርቆስ ከተማ እየተቃረብን መሆኑን ስረዳ የሆነ የቁጭት ስሜት ተሰማኝ፡፡ ለምን ከባህር ዳር ጀምሮ ላዋራው አልሞከርሁም? ደደብ ነህ ሲሳይ! አልኩት እራሴን፡፡
እየነካካሁት ያለውን ስልኬን ለአፍታ አስቀምጬ ወደ ሰዉየው ዞር በማለት፡-
‹‹የምሬን ነው ጋሼ ያን ያህል እርቀት ካንተ ጋር መነጋገር ባለመቻሌ የትም የማላገኘው ብዙ እዉቀት እንደቀረብኝ ተረዳሁ›› አልኩት፡፡
ትንሽ ፈገግታ ካሳየኝ በኋላ፡-
‹‹…እንዲያዉም አንተ በጣም ጎበዝ ልጅ ነህ፤ ብዙ ነገር ተጨዋወትንኮ›› ካለኝ በኋላ ለመሆኑ የትኛውን የትምህርት ዘርፍ ነው ያጠናህ?›› ሲል ጠየቀኝ፡፡
‹‹ጋዜጠኝነት››
‹‹ለዚያ ነዋ!›› ብሎ ይበልጥ ፈገግ ሲል አየሁት፡፡
‹‹…ይገርምሃል! እንደዚህ እንደ ዛሬው መንገድ ስወጣ መጽሃፌን ከማገላበጥ ዉጭ እምብዛም ሰዎች ጋር ወሬ የማዉራት ልምድ የለኝም፡፡ አንተ ግን እኔን አግባብተህ ለማዋራት ያደረግኸው ጥረት ገርሞኛል፡፡ ለዚያም ነው ምንድን ነው ያጠናኸው ብየ የጠየቅሁህ፤ አንተማ ዋናው ስራህ ነዋ፤ ማለቴ… እንደዚህ ሰውን አግባብቶ ምስጢር እንዲዘከዝክ ማድረጉ…›› ብሎ እንደገና ሲስቅ እኔም አብሬው ለመሳቅ ሞከርሁ፡፡
በዚህ ሁኔታ በደንብ ከተግባባን በኋላ ሁለታችንም በየፊናችን የተላክንበትን ተልዕኮአችንን አጠናቀን ወደ ባህር ዳር ስንመለስ ድጋሜ ልንገናኝ እንዲሁም አንዳንድ ስራዎችን አብረን እንደምንሰራ ተነጋግረን ስንጨርስና መኪናው ደብረ ማርቆስ ከተማ ሲደርስ አንድ ሆነ፡፡ ከአዉቶቡሱ ወርደን ጥቂት እርምጃዎችን በእግራችን ስንጓዝ ‹‹ግንኮ ጋሼ! ስምህን አልነገርከኝም›› ስል ጠየቅሁት፡፡
‹‹እናንተ ጋዜጠኖችኮ ፊት ከሰጧችሁ አትቻሉም›› ብሎ ረጅም ሳቅ ድጋሜ ከሳቀ በኋላ ‹‹እሺ!…ሙሴ እባላለሁ፡፡ በአንጋፋው የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለሃያ ስምንት አመት ያህል አስተምሬያለሁ፡፡ አሁንም እያስተማርኩ ነው፡፡ በሀገራችን የስርዓተ ትምህርት አሰጣጥ ዙሪያ እጅግ ብዙ ጥናቶችን በግሌና ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ሰርቻለሁ፡፡ የዶክትሬት ዲግሪየን የሰራሁት ከዛሬ ሃያ አመት በፊት ነው፡፡ ከስምንት አመት በፊት ደግሞ ዩኒቨርሲቲው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቶኛል… ተግባሬ እኔን እንዲገልጸኝ እንጂ ‹እኔ ማለት እንዲህ አይነት ሰው ነኝ› ማለት ባህሪየ ስላለሆነ ከስራ ባልደረቦቼና አጋሮቼ ዉጭ በብዙዎች ዘንድ አልታወቅም፡፡ ሚዲያ ላይ መናገር ስለማልደፍር አንተም ቢሆን አታዉቀኝም›› ብሎኝ ድጋሜ ለመለያያ ሰላምታ እጁን ዘረጋልኝ፡፡
ሰዉየው ስራዉንና ማዕረጉን ሲነግረኝ የሆነ ሃፍረት ሽምቅቅ ሲያደርገኝ ታወቀኝ፡፡ እንዴት ግን አላወቅኋቸውም? እንዴት ግን ‹‹አንቱ›› ብየ አላዋራኋቸውም? እንዴት ያለ ልማዴ ሰዉን ማክበር ተሳነኝ? እኚህን የተከበሩ ምሁር… ለሃያ ስምንት አመታት ያስተማሩ ታላቅ ሰው… በሺዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ያፈሩና ለወግ ለማዕረግ ያበቁ… ለሃገራችን ፋይዳ ያላቸው ብዙ ጥናቶች ያበረከቱልንን እንቁ ዶክተርና ፕሮፌሰር ስማቸውን አንጠልጥየና የክብር ካባቸውን ገፍፌ ‹‹አንተ›› እያልኩ በማዋራቴ ከዉስጤ የመነጨ ሃፍረት ተሰማኝ፡፡
መቼም እኛ ሰዎችን በእድሜያቸውና በሽበታቸው ሳይሆን በጀብዷቸው ክብር መስጠት ነው የሚቀናን፡፡ ይሄ የሰፈራችን ሃቅ ነው፡፡ የሰማኒያ አመት የእድሜ ባለጸጋ ጉዳይ ለማስፈጸም ቀበሌ በወረፋ ተሰልፈው እኛ ግን የደንብ ማስከበር ልብስ የለበሰውን ወጣት ወረፋው እንዲቀድም እናሸረግዳለን፡፡ እድሜ ወገባቸውን ካጎበጣቸው አዛውንቶች ይልቅ እፍኝ ለማትሞላ ስልጣን ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡ አይ እኛ! እያልኩ እራሴንና ሌሎችን እየታዘብሁ ነበር ከማርፍበት ሆቴል የደረስኩት፡፡
የማረፊያ ክፍሌን ካመቻቸሁ በኋላ አልጋየ ላይ ጋደም እንዳልኩ ቀን ላይ ከፕሮፌሰር ጋር ያወራናቸውን እንደ ከረሜላ የሚጣፍጡ አንዳንድ ንግግሮች እያስታወሰኩ ማስታወሻየ ላይ ልከትባቸው ሞከርሁ፡፡ ፕሮፌሰር የተናገሯቸው ቃላቶችና የሚያስተላልፉት መልዕክት አንዳቸውም የሚወድቁ አልነበሩም፡፡ ውድ ዋጋ የሚያወጡ ንብረቶች ያህል ዋጋ ነበራቸው፡፡
ክፍል 2 ይቀጥላል......
****
ከ "ሁለቱ ማዶዎች" መፅሐፍ የተወሰደ

Comments
Post a Comment