የከሸፈ ትውልድ 2
ክፍል 2 - Part 2
ከወራት በኋላ የቀን ዉሎ ማስታዎሻየ ላይ የተጻፉ ነገሮችን እያገላበጥኩ ስመለከት የፕሮፌሰሩን ንግግሮች አገኘኋቸው፡፡ ጊዜ መስጠት አልፈለግሁም፤ ወዲያው ስልኬን አዉጥቼ ለፕሮፌሰር ደወልኩላቸው::
ከፕሮፌሰር ሙሴ ጋር ከዩኒቨርሲቲው ግቢ ዉስጥ ከሚገኘው የመምህራን መዝናኛ ክበብ ቡና እየጠጣን ብዙ ነገሮችን ተጨዋወትን፡፡ ለዛሬው ብዙ አድማጭ እንጂ ብዙ ተናጋሪ አልነበርኩም፡፡ የዩኒቨርስቲው ግቢ ደስ ይላል፡፡ ከመንገዱ ዳርና ዳር የሚገኙት ዛፎች ቅርንጫፍ ለቅርንጫፍ ተቃቅፈዋል፡፡ በዚያ ላይ ቅዝቃዜው፡፡
ቀጭኑን የአስፋልት መንገድ የግራ ጠርዝ ይዘን ከፕሮፌሰር ጋር ወደ ግቢው መሃል ዘለቅን፡፡ ግቢው አድሮ አዲስ ነው፡፡ ሲያምርና ሲፈካ ነው የሚያድረው፡፡ የተማርኩበት ግቢ… በተለምዶ ጆኮ ስኩል /Joco school/ ተብሎ የሚጠራው ህንጻ… አለፍ ሲል የተፈጥሮ ሳይንስ ቤተ መጽሃፍት… እነዚህ ብቻ ናቸው ባሉበት ያገኘኃቸው፡፡ ያኔ ተማሪዎች እያለን እንደነበረው ከነ ሙሉ ዉበታቸው አሉ፡፡ አዲስ ነገር የተጨመረው ከቤተ መጽሃፍቱ ጎንና ዙሪያውን የተሰሩት የብረት ጠረንጴዛና ወንበሮች ናቸው፡፡
‹‹…ተመልከት ይሄ ሰነፍ ተማሪዎች እንደ አሸን የሚፈሉበት ዋሻ ነው›› አሉኝ ፕሮፌሰር፤ ተማሪዎቹ አንድ ለአምስት እየተደራጁ ወደሚወያዩበት ክብ ሰርተው የተደረደሩ ወንበሮች እንድመለከት እየጋበዙኝ፡፡
ቤተ መጽሃፍቱ አካባቢ በሚገኙት አረንጓዴ ዛፎች መካከል ባሉት ክፍት ቦታዎች አለፍ አለፍ ብለው በወንበሮች የተከበቡ ሰፋፊ የላሜራ ጠረንጴዛዎችን ስመለከት እዚያ ላይ ተቀምጦ ጥናት ማጥናት ምን ያህል የንባብ ፍላጎትን ሊቀሰቅስ እንደሚችል እያሰብኩና እየጎመጀሁ ነበር፡፡ ወንበሮቹም ሆኑ ጠረጴዛዎቹ ዉሃ ሰማያዊ ቀለማት ያሏቸው ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር የማንበቢያ ቦታዎችን በምን ምክንያት እንዲህ ዝናቸውን እንዳቀለለው ስላልገባኝ እንዲያስረዱኝ ጠየቅኋቸው፡፡ አንደኛውን ጠረጴዛ ዙሪያውን ከበው በአንድ ለአምስት ተደራጅተው መጽሃፍና ሃንድአዉት የዘረጉትን ተማሪዎች እየጠቆሙኝ፡-
‹‹አሁን እንዲህ ዙሪያ ጥምጥም ተቀምጠው ሲታዩ የሚሰሩ ይመስልሃል አይደል?›› ሲሉኝ በአዎንታ አንገቴን ነቀነቅሁላቸው፡፡
‹‹…በአብዛኞቹ በአንድ ለአምስት ተደራጅተው የሚወያዩ ቡድኖች ላይ ባደረግነው ጥናት በቡድን የተሰጡትን አሳይመንት ወይም የቤት ስራ የሚሰራው በአንድ ወይም በሁለት ተማሪዎች ብቻ እንደሆነ ደርሰንበታል፡፡ ሞካሪው ተማሪ መልሱን ይሰራዉና ከዚያ በኋላ የሌሎች ተማሪዎች ስም የቤት ስራዉን እንደሰሩ ተደርጎ ይመዘገባል፡፡ ከዚያም ሌሎች የቡድኑ አባላት የልፋቱን ዋጋ ገንዘብ አዋጥተው ይከፍሉታል፡፡ በዚህ አሰራር አብዛኞቹ ተማሪዎች የቢዝነስ ሰዎች ሆነው አርፈዋል፡፡ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይም ይሄ ሁኔታ በስፋት እንደሚታይ በጥናት አረጋግጠናል፡፡
መምህራን እራሳቸው በዚህ የተማሪዎች የአንድ ለአምስት ስራ ላይ ያመኑበት አይመስልም፡፡ ለይስሙላና ለሪፖርት ብቻ ‹የተወያያችሁበትን በቃለ ጉባኤ አጽድቃችሁ ቢሮ ድረስ አምጡልኝ› ብለው ተማሪዎችን ጥለዋቸው ይሄዳሉ፡፡ ዉጤቱ ደግሞ ያው ነው፡፡ በአንድ ወይም በሁለት ተማሪዎች መልሱ ተሰርቶ ለመምህሩ ይላክለታል፡፡ የቤት ስራዉም ሆነ የክፍል ስራዉ በእንደዚያ መንገድ ነው የሚሰራው፡፡
ተመልከት! በዚህ ሁኔታ የሙስናና የኪራይ ሰብሳቢነት ጽንሰ ሃሳብ የሚጠነሰሰው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዉስጥ ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ እና በዚህ አሰራር ህጻናት ነጭ ወረቀት በሆነ አዕምሮአቸው ላይ ሙስናን ጽፈዉበት የሚወጡት እዚህ አይደለም ትላለህ?›› ብለዉኝ ለደቂቃዎች ጸጥ አሉ፡፡
እዉነት ነው አልኩ፡፡ ይሄንን ርዕሰ ጉዳይ ጥቅሙን እንጂ የጎንዮሽ ክፍተቱን አንድም ቀን እንዲህ በጥልቀት አስቤው አላዉቅም ነበር፡፡ ፕሮፌሰር ከጸጥታቸው ተመልሰው ንግግራቸውን ቀጠሉ፡-
‹‹…እንደ እድል ሆኖ ይቺ ሀገር የሰጧትን መቀበል እንጂ የራሷን ማጎልበት አታውቅበትም፡፡ ቢ ፒ አር ተባለ… ቢ ኤስ ሲ ተተገበረ…
አንድ ለአምስትን ከአጸደ ህጻናት እስከ ዩኒቨርስቲዎቻችን፣ ከአስፈጻሚ ቢሮዎች እስከ አርሶአደሮች ቀየ ተገበርነው፡፡ ‹ለዉጡ ምን ሆነ?› ብሎ ያጠናውና ያስተካከለ አካል ግን የለም፡፡ አንድ ለአምስት ለሃገራችን የፈየደው
ምንድን ነው? እስከሚገባኝ አንድ ለአምስት የተለየ ወይም ወጣ ያለ ሀሳብ ያላቸውን ሰዎች ለማጥመድ የተነደፈ ድራማ ነው፡፡ በአጠቃላይ
ሰው ተመሳሳይ አስተሳሰብ እንዲኖረው የተነደፈ መርህ ይመስላል፡፡ ተመሳሳይ የሚያስብ ሰው ደግሞ ከእንስሳ በምንም አይለይም፡፡ አዲስ
ነገርን መፍጠር አይችልም፡፡ ሰዎች በስራ ቦታቸው፣ በስልጣናቸውና በእምነት ቦታዎች ሳይቀር በጥርጣሬ እንዲተያዩ፣ አንዱ ሌላውን
እንዳያምነው የሚያደርግ ፍልስፍና ነው፡፡ እና አንድ ለአምስት እንኳን ከሰዉ ከተፈጥሮ ጋርም ይጋጫል፡፡
የሚገርመው ነገር የመጣዉን ሁሉ እየተቀበልን እንደ ላም ወተት መጋታችን ነው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ግን ‹‹ሲስተሙ ለሃገራችን እድገት ስላልበጀ ተቀይረሯል›› ይባላል፡፡ ሳይጀምሩ መጨረስ ይሉሃል ይሄ ነው፡፡ ጠቃሚ ቢሆን እንኳን በጉዳዩ ዙሪያ የሚመለከታቸው አካላት ትንታኔና ገለጻ የሚሰጡበት የተመቻቸ መንገድ የለም፡፡
አንድ ቀላል ምሳሌ ልስጥህ- እንደኔ አይነቱ አንድ ዶክተር ይነሳና ጫትና ሲጋራ ጎጅ ነው… ለሱሰኝነት ያጋልጣል… በመጨረሻም ለሞት ይዳርጋል…! እያለ ሲያስተምር ታያለህ፡፡ ‹ለምን ይጎዳል? የሚል ጥያቄ ሲነሳ ግን መልስ አልባ ይሆናል፡፡
ጫት በአካባቢያችን ከሚገኙ ቅጠሎች እንደ አንዱ ነው፡፡ ታዲያ ለምን ሱስ ያስይዛል? ለምን ሰዉን ይጎዳል? ለምንስ የምግብ ፍላጎትን ይቀንሳል? በወረቀት ላይ ከተጻፈው የዘለለ በተግባር የተረጋገጠ መልስ የሚሰጠን ባለሙያ ግን የለም፡፡ ጫት ጎጂ እንደሆነኮ ሺህ አመት ተወርቶለታል፡፡ በመማሪያ መጽሃፎቻችን ሳይቀር በተደጋጋሚ ታትሟል፡፡ የጫትን ጉዳት አጥንቶ ይሄንን ያህል አሲድ ስለያዘ… ይሄን ያህሉ ደግሞ አነቃቂ ስለሆነ… ቀሪው ደግሞ የመመረዝ ባህሪ ስላለው ብሎ በተግባር እያሳየ የሚያረጋግጥልን ባለሙያ ግን የለንም፡፡ በተቃራኒው እራሳቸው ጫት እየቃሙ ሌላውን የሚከለክሉ፣ በየደቂቃው ሲጋራ እያንቦለቦሉ ሌላውን የሚያወግዙ መካሪዎችን ነው የምንመለከተው- እኔን ጨምሮ፡፡
ዩኒቨርስቲዎቻችንን ተመልከት፤ በዘመናዊ መሳሪዎች የተደራጁና የሚያስንቁ ቤተ ሙከራዎችን /ላቦራቶሪዎችን/ ገንብተው በዉስጣቸው አቅፈው ይዘዋል፡፡ እስካሁን ግን የእኛ የሆኑትን የሃበሻ አረቄ፣ ጠላና ጠጅ… የአልኮል መጠናቸውን አረጋግጠው ሊነግሩን አልቻሉም፡፡ ‹ለምን?› ብለህ ብትጠይቅ እነሱም መልስ የላቸውም፡፡
ዛሬ ድረስ የፈረንጅ ቢራና ዉሰኪ ፎርሙላ ከጠርሙሱ ላይ አንብበው የኮረጁትን ይነግሩናል፡፡›› ብለው ሲጋራቸውን ከኮታቸው ኪስ ፈርፍረው አወጡ፡፡ ሲጋራ ያጨሳሉ ብየ አልገመትኩም ነበር፡፡ ደነገጥኩ፡፡ ፕሮፌሰር ለምን ያጨሳሉ? ብየ ልጠይቃቸው አሰብኩና ሌላ መልስ አልባ ክርክር መክፈት ስላልፈለግሁ ተዉኩት፡፡ ወዲያው አፌ ላይ እንደመጣልኝ ‹‹የሚገርመውኮ ፕሮፌሰር ለዉጤታማ ስራ የምንጠብቃቸው ምርጥ ልጆቻችንም የባዕድ ሃገር ናፋቂዎች ሆነዋል፡፡
እዚህ ስንት ገንዘብ ፈሰስ ተደርጎላቸው ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ እጃቸውን አጣጥፈው ምንም ሳይሰሩ ይቆያሉ፡፡ ይቺን ምስኪን አገር ሲለቁ ግን ተአምር የሚያሰኙ ቴክኖሎጂ ዉጤቶችን ይሰራሉ፡፡ ለሀገራቸው የነፈጓትን እዉቀትና ችሎታ ከሃገር ሲወጡ ከጭንቅላታቸው ያፈነዱታል፡፡ ይቺ ሀገር ታዲያ እንዴት ነው የምታድገው? እኛ ልጆቿ በልቶ ካጆች ሆነን አለቅንኮ!›› አልኳቸው፡፡ የዉስጤን ስሜት ነበር ሳላስበው የተነፈስኩት፡፡
‹‹…ልክ ነህ፤ ግን የእነሱ ስህተት አይመስለኝም፡፡ ሀገሪቷም ችግር አለባት፡፡ እነዚህ የምትላቸው ወጣት ምሁራን ሀገር ዉስጥ በወረቀት የነደፉትን የፈጠራ ሃሳብ ወደ ተግባር ሊሞክሩት ሲያስቡ እብዶች ናቸው! ቅዠታሞች ናቸው! ትላቸዋለች፡፡ ‹‹ገንዘቤን ጠልቼዋለሁ ወይ ከእነዚህ ጋር አብሬ የምሰራ…›› የሚለው ወሬኛ ይበዛል፡፡
ጥቂቶቹ ይህንን ሁሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው፣ የሰሙትን እንዳልሰሙ አልፈው ጥናታቸውን እውን ለማድረግና ወደ ተግባር ለመቀየር ይሞክራሉ፡፡ ያኔ ከቀበሌው ሊቀመንበር እስከ አገር ሽማግሌዎች ተመርጠው ጉብኝት፣ ገለመኔ እያሉ ብቻዉን አፈር ግጦና ለፍቶ በሰራው ስራ የማይመለከታቸው አካላት ጣልቃ ገብተው ለሚዲያ ገለጻ ያደርጋሉ፡፡ ‹‹ይህ ወጣት የሰራው ስራ ለሌሎች ስራ አጥ ወጣቶች ሞዴል ነው›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ሙከራዉን ለማህበረሰብ ጠቃሚ ስለሆነ አስፋፍቶ እንዲሰራ ድጋፍ እንደሚያደርጉለት ይቦተለካሉ፡፡ በዚያም በዚህም የተስፋ ዳቦ ያበስሉለታል፡፡ በማግስቱ ግን ዙረው እንኳን አያዩትም፡፡ ከነ አካቴውም መኖሩን ይረሱታል፡፡ ሚዲያዉም አብሮ ይረሳዋል፡፡ ሳስበው ይቺ አገር እራሷ በምትተውንበት ኮሜዲ ድራማ ነው መልሳ የምትስቀው፡፡
በዚች ሀገር ሂሳብኮ ምን ያህል ለማህበረሰቡ ጠቃሚና ለዉጥ የሚያመጣ ጥናት ብትሰራ ከመጤት የሚቆጥርህ የለም፡፡ ለችግሮች ሁሉ መልስ የሚያመጣ ተብሎ የሚታሰበው ጊዜ ያለፈበት የአዉሮፓ፣ የኢዢያና የአሜሪካ ፈላስፎች የቅዠት ጽሁፍ ነው፡፡ እነሱ ሌሊት ይቃዣሉ፣ ቅዠታቸውን ሀገራቸው ባትቀበለው እንኳን እንደ ህዝብ ሽንት ቤት የሚጸዳዱባት ‹አፍሪካ› የተሰኘች ምስኪን የቅዠት ማራገፊያ አህጉር አለችላቸው፡፡
‹እንትና የተባለው የኤስያ ፈላስፋ እንደተናገረው…›
‹እገሌ የተሰኘው የአሜሪካ ተመራማሪ እንዳረጋገጠው…›
‹እገሊት የተባለችው ታዋቂ ምሁር እንደጻፈችው…› እየተባለ የባዕዳን ሀገር ፍልስፍና ትጠጣለህ፡፡ አውሮፓዉያንና አሜሪካዉያን ግን ቅዠታቸውን ወደ ህልም ህልማቸውን ወደ ተግባር ለውጠው ተጠቅመዉበታል፡፡ ያኔ ድሮ ላይ እራሳቸውንና ሃገራቸውን ቀይረዉበት አልፈዋል፡፡ እኛ ነን በራሳችን አልጋ ተኝተን የነሱን ቅዠት እስካሁን ድረስ የምንቃዥላቸው፡፡
የምናስተምራቸው ተማሪዎች መመረቂያ ጽሁፍ እንዲሰሩ ስናደርግ እንኳን ለማህበረሰቡ ችግሮች መፍትሄ እንዲያመጡ ታስቦ ነው፡፡ ነገር ግን ቀደም ብየ እንደነገርኩህ ማጣቀሻቸው በሙሉ የአዉሮፓና የኤዢያ ፈላስፎች ቅዠት ነው፡፡ እንደ ብር ነጥረው እንደ ወርቅ ተፈትነው የወጡትን የሃገራችንን ምሁራን ጥናቶች እንኳን ለጽሁፋቸው ግብአትነት እንዲጠቀሙ እኛ መምህራን ተማሪዎቻችንን አናበረታታቸውም፡፡ በተቃራኒው
የሃገራችን ምሁራን የሰሩትን ጥናት በማጣቀሻነት ሲጠቀሙ እንዘባበትባቸዋለን፡፡
አንዳንዴ አላዋቂነታችን ብቻ ሳይሆን ምቀኝነታችን ጭምር ጎልቶ ይወጣብኛል፡፡ ለዚህኮ ነው ስንት ገንዘብና ጉልበት፣ እዉቀትና ጊዜ የፈሰሰባቸው የተመራቂ ተማሪዎችን የጥናት ዉጤት ፍሬ አልባ ገለባ ብቻ ሆነው የሚቀሩት! ለዚህኮ ነው ጥናቶቻችን ሁሉ የኩረጃና የስርቆት የሚሆኑት፡፡
ተመልከት! ሀገሪቱ ስንት ለፍታ እዚህ ያደረሰቻቸው ተማሪዎች አብዛኞቹ ከነገርኩህ የበለጠ አካሄድና ህይወት የላቸውም፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ‹በዲግሪ ያስመርቃሉ› ከሚባል ‹የዲግሪ ወረቀት ያድላሉ› ቢባል ይቀላል፡፡ የትምህርት ፖሊሲያችን በራሱ የቁጥር ብዜት ዉጤት ነው፡፡ ለሪፖርት ብቻ ‹በዚህ አመት ይሄን ያህል ሺህ ተማሪዎችን አስመረቅን› ሲሉ ይደሰኩሩብናል፡፡ ለዚህኮ ነው ዲግሪው እራሱ እንደ ገንዘባችን ዋጋ አልባ የሆነው፡፡
በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ‹ዲግሪ እንደ ጉድ ይታፈስባታል› ተብላ የምትታማውን ህንድን በወፍ በረር እንመልከታት፡፡ ህንድ በተመሳሳይ የትምህርት መስክ አራት አይነት ተማሪዎች አሏት፡፡ ተማሪዎችን እንደ ዉጤታቸውና ትምህርት አቀባበላቸው መድባ በአራት የተለያዩ ክፍሎች ታስተምራቸዋለች፡፡ በመጀመሪያው ክፍል እጅግ ጎበዝ የሆኑ ተማሪዎች ይመደባሉ፡፡ በሁለተኛው ክፍል ደግሞ በውጤታቸው ከመጀመሪያዎቹ ዝቅ ያሉ እንዲሁም በሶስተኛው ክፍል መለስተኛ ውጤት ያላቸው ተብለው በቅደም ተከተል ተመድበው ይማራሉ፡፡
ታዲያ በመጀመሪያውና በሁለተኛው ምድብ ተምረው የላቀ ዉጤት የሚያመጡትን ተማሪዎች ምንም ያህል ቢሆን ዋጋ ከፍላ እዉቀታቸውን በሃገራቸው እንዲያፈሱት ታደርጋለች እንጂ ወደ ዉጭ እንዲሰደዱ አትፈቅድም፡፡ እዚህ የምታያቸውና በየሃገሩ የተበተኑት የህንድ መምህራንና ባለሙያዎች ከጥቂቶቹ ዉጭ አብዛኞቹ በዝቅተኛ ዉጤት የተመረቁ አሊያም የዉሸት ዲግሪ አሰርተው የመጡ ናቸው የሚባለውም ከእዉነት የራቅ ላይሆን ይችላል፡፡ እኔ ይቅርታ አድርግልኝና ፖሊሲዎቻችንና ስትራቴጅዎቻችንም በአብዛኛው ቀዳዳ ደፋኞች አይደሉም፡፡
ስልጠናዎቻችንን ተመልከታቸው፤ ለሪፖርት ፍጆታ ብቻ ነው የሚዉሉት፡፡ በኤች አይ ቪ ኤድስ እየተማገደ የሚነደው ወጣቱ ሆኖ እያለ ስለ ኤች አይ ቪ ኤድስ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች ስልጠና የሚሰጠው ለሃማኖት አባቶችና ለካቢኔ አባላት ነው፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ወጣቱ ግን እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ እሳቱ ላይ ተጥዷል፡፡ ይሳሳማል… ይዘሙታል… ይቃጠላል… ይነዳል፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን የሃይማኖት አባቶች ቤተ አምልኮአቸውን ዘግተው ፓርላማ ለመመረጥ ትግል ላይ ናቸው፡፡ የመንግስት አካላትም ቢሆኑ ስለ በሽታው መልዕክት የሚያስተላልፉበትና ግንዛቤ የሚፈጥሩበት ቅንጣት ጊዜ የላቸውም፡፡ እነሱ ሁሌም መልስ በሌለው ስብሰባ እንደተጠመዱ ናቸው፡፡ እነሱኮ የዉሎ አበል ለቀማ ላይ ነው ትኩረታቸው ያለው፡፡
ባለፈው መንግስታችን ለስደት ተመላሾች የተሻለ ነገር እንዳመቻቸላቸው ይፋ አደረገ፡፡ በፈቃድም ይሁን በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ሃገራቸው የተመለሱ የስደት ተመላሾች ሁሉም ባይሆኑም የተወሰኑት የተገባላቸው ቃል ተፈጻሚ ሆነላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ንግድ እንዲጀምሩና በሀገራቸው እንዲሰሩ ከተማ ዉስጥ የመስሪያ ቦታና መሰል ድጋፍ ተደረገላቸው፡፡ ይሄ ምን ያነሳሳ ይመስልሃል? ይባስ ብሎ ለህገወጥ ስደትና ከሀገር ለመዉጣት ያቆበቆቡ ወጣቶች ተፈጠሩ፡፡
ምክንያቱ ምን መሰለህ? ‹በተወለድንበት ሃገር ባደግንበት ቀየ ዞሮ የሚያየን አካል የለም… እንደ ዜጋ አንቆጠርም… የመስሪያ ቦታ የለንም… ስለዚህ ተሰደን ስንመለስ እንደ ዜጋ ከተቆጠርንና ድጋፍ የሚደረግልን ከሆነ ለምን እዚህ እንቀመጣለን? ለምን አንሰደድም? ወይ ያልፍልናል አልያም ስመለስ እዚሁ ያልፍልናል…› ብለው ስደትን እንደ አማራጭ የሚቆጥሩ ወጣቶች ተፈጠሩ፡፡
ለዚች ሃገር እድገት የሆነ መስዋትነት ሳይከፍል ያለፈ ትዉልድ ያለ ይመስለኛል፡፡ አባቶቻችን ለዳር ድንበራቸው የተዋደቁትን ያህል ለአንድነታችን አልሞቱም፡፡ ችግሩ ግን ምንድን ነው? ፖለቲካ? ሃይማኖት? ባህል? የትምህርት አሰጣጣችን ድክመት ወይስ ሌላ ምክንያት? ይሄ እራሱ ግልጽ አልሆነልንም፡፡
የትም የአለም ሃገራት ብትሄዱ ሃገራቱ የራሳቸው የሆነ መሪ ቃል /moto/ አላቸው፡፡ የኛ ሃገር አነሳሽ መፈክርስ ምንድን ነው? እምነትና ማንነትን ባህልና ሃይማኖትን አዋህዶ ወደ እድገት የሚመራን መፈክራችን ምን የሚል ነው? አየህ! ለጥያቄው መልስ የለውም፡፡ እኛ ማለት መፈክር አልባ ህዝቦች ነን፡፡ ደርግ እንኳን ቢሳካም ባይሳካም ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም!›› እያለ ይፎክርና ያስፎክር ነበር፡፡
‹ቅድስት አገር› እያልን ያለቅድስናዋ ወደምናሞካሻት አሜሪካ በወፍ በረር ምናባችንን እንላክና እንዳሳት፡፡ በእያንዳንዱ አሜሪካዊ ቤትና ቢሮ ዉስጥ የሃገሩ ሰንደቅ አላማ በጉልህ ይታያል፡፡ ለአሜሪካዉያን ሰንደቅአላማ ማለት መገለጫቸው ነው፡፡ ዜጋው ቤቱ ዉስጥ ሰንደቅ አላማ ከሌለ ሌላው ህይወቱ ባዶ እንደሆነና ለአሜሪካ ልጇ ሳይሆን የእንጀራ ልጇ እንደሆነ አድርጎ እራሱን ይቆጥራል፡፡ አሜሪካዊነቱን በፈቃዱ እንደተቀማ አድርጎ ያስባል፡፡
እኛ ዘንድስ? ስንቶቻችን ቤት ዉስጥ የሃገራችን ሰንደቅ አላማ ይኖር ይሆን? እንዲያው አጋነንከው አትበለኝ እንጂ አገሪቷስ ቢሆን ህዝቦቿን በሙሉ ያስማማ ሰንደቅ አላማ አላት? እደግመዋለሁ! አገሪቷስ ቢሆን ህዝቦቿን በሙሉ ያስማማ ሰንደቅ አላማ አላት ወይ? ልጆች ሆነን ትምህርት ቤት ስንማር እንባችንን እያፈሰስን በስሜት የምንዘምረው አንድ መዝሙር ነበር፡-
ባንዲራችን…
ባንዲራችን…
አረንጓዴ ቢጫ ቀይ፤
አርማችን ነው…
መለያችን…
የኢትዮጵያ ሃገራችን፤
ባንዲራችን /2/
አረንጓዴ… ቢጫ… ቀይ…
ይሄን መዝሙር የቱንም ያህል ጊዜ ደጋግመህ ብትዘምረው ‹‹አረንጓዴ ቢጫ ቀይ›› ይላል እንጂ ከመካከል ሰማያዊ ኮከብ አይልም፡፡ ለዚህ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቅ፣ ለአንዲት ኢትዮጵያ ሲል ቴዎድሮስ ተሰዉቶላታል፡፡ ምኒሊክ ከወራሪ ከጠላት ጋር ተዋድቋል፡፡ ዮሃንስ ከድርቡሽ ጋር ተፋልሞ ህይወቱን ገብሯል፡፡ በላይ ዘለቀ ህይወቱን ሳይሰስት ከፍሎላታል፡፡ አብዲሳ አጋ ታስሮላታል፡፡ አሉላ አባ ነጋ ተሰቃይቶላታል፡፡ በአጠቃላይ ጀግኖች የማይሆነውን ሆነውላታል፡፡
በሚያምረው አርማችን ላይ ሰማያዊ ኮከብ አምጥተን ስንደነቅርበት ግን አሁን የገጠመን ነገር ሆነ፡፡ አንድነታችንን አፈረሰው፡፡ የተዋደድነውን አጣላን፡፡ የተጋባነውን አፋታን፡፡ የተሰባሰብነውን በታተነን፡፡ ይኸው በህብረቀለማቱ ሳይሆን በአንዱ ቀለም መመካት ጀመርን፡፡ አንደኛው አረንጓዴውን ይፈልጋል፡፡ ሌላኛው ‹‹ቀዩ የኔ ነው!›› ማለት ጀምሯል፡፡ ቀሪው ደግሞ ‹‹ቢጫው ለእኔ ይገባኛል›› ሲል ይጠይቃል፡፡ ኮከቡን የሚፈልግና ለኮከቡ የሚዋደቅ ትዉልድ ግን እስካሁን አላየሁም፡፡ እንዲያዉም ኮከቡ ሲወራ የሚያንገፈግፈው ትዉልድ ተፈጥሯል፡፡
ይቀጥላል........
ከ"ሁለቱ ማዶዎች" መፅሀሐፍ የተወሰደ
Comments
Post a Comment