የከሸፈ ትውልድ 3

የመጨረሻው ክፍል Last Part

ከዚህ ርዕስ ሳልወጣ አንድ ወርክሾፕ ላይ የታዘብኩትን ገጠመኝ ላካፍልህ፡፡ አወያዩ የሆነ ጠንከር ያለ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ሲያወያዩን ከቆዩ በኋላ ‹…እስኪ ቤታችሁ ዉስጥ የእናት ሀገራችሁን ሰንደቅ አላማ የሰቀላችሁ ወይም ያስቀመጣችሁ?› ብሎ ጠየቀ፡፡ ከአዳራሽ ሙሉ ተሰብሳቢ መካከል አንድ እንኳን ‹እኔ› ብሎ እጁን ያወጣ አልነበረም፡:
(የክፍል 2 ሊንክ )
ሰዉየው በአግራሞት እየተመለከተን ‹ባንዲራ ቤቱ ያለው የለም?› ሲል ድጋሜ ጠየቀ፡፡ አሁንም ጸጥታ እንጂ ምላሽ አልነበረም፡፡ ሰዉየው ፈገግ ብሎ ንግግሩን ቀጠለ ‹እሽ! የድሮው ባንዲራም ቢሆን?› ሲል ሶስት እድሜ ጠገብ አባቶችና ብዛት ያላቸው ወጣቶች እጃቸውን አወጡ፡፡ ከአጠገቤ የተቀመጠ አንድ ወዳጄ ‹አየህ በሰንደቅአላማችን እንኳን አልተስማማንበትም፤ ይገርማል! የዚች እንቆቅልሽ የሆነች አገር ጉዳይ!› ያለኝን አልረሳዉም፡፡ የሆሊዉድና ቦዉሊድ ፊልም ሰሪዎች ፊልማቸው ዉስጥ አንድም ቀን ስለ እርሻ ስራቸው፣ ስለ አዘራራቸውና ስለ ምርት አሰባሰባቸው አሳይተዉን አያዉቁም፡፡ በተቃራኒው ግን የቡድን ወሲባቸውን፣ ባዕድ አምልኮታቸውንና መረን የለቀቀ ተግባራቸውን ያስኮመኩሙናል፡፡ ዝሙትን፣ ሱስን፣ ስርቆትንና መገዳደልን ይግቱናል፡፡ ተንኮላቸውን እያሰረጹብን እንደሆነ ግን የሚረዳ ትዉልድ የለም፡፡ ግዕዝ ቋንቋችን በጠራራ ፀሃይ ሲዘረፍ ‹‹የዘራፊ ያለሽ ኡ ኡ›› ብሎ ድምጹን ያሰማ አካል የለም፡፡ ከእኛው ምድር በቅሎ ለዘመናት የተመገብነውን ጤፋችንን አይናችን እያየ ‹‹ባለቤት አይደላችሁም፤ ባለቤቶቹ ኔዘርላንዶች ናቸው!›› ስንባል ‹‹ትክክል ናችሁ›› በሚል አይነት እግራችንን አጣጥፈን ተቀምጠናል፡፡ ምን አዚም እንደተደረገብን አላዉቅም፡፡ እነሱኮ የበይ ተመልካቾች አድርገውናል፡፡ የእኛ የሆነውን ጥምቀትና መስቀል አርክሰን፣ ገና ጨዋታዉን ገድለን ለእነሱ እንድንዘምር አድርገውናል፡፡ ወጣቱ ስለ አርሴናልና ማንቼ ቆስሏል… ስለ ቸልሲ ተፈናክቷል… ስለ ሊቨርፑል ደምቷል… አምናና ዘንድሮም ወጣቶቻችን ኳስ ለማየት ዲ ኤስ ቲቪ ቤት ሰልፍ ላይ ናቸው፡፡ ኳስን ተመልክቶ አለፍ ሲልም ኳስ ተጫዉቶ የኢትዮጵያን እግር ካስ የታደገ ወጣት ግን ማየት አልተቻለም፡፡ ትናንትናም ይሁን ዛሬ እግር ኳሳችን የአለም መጨረሻ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በእርግጥ ኳስ ለታፈነ ህዝብ ጥሩ ማስተንፈሻ ነው፡፡ በኮማንድ ፖስትና በአዋጅ የታፈነ ህዝብ ንዴቱ የሚያልፍለት ማታ ላይ ኳስ እየተመለከተ በሚጮኸው ጩኸት ነው፡፡ የአድዋ ድላችንን ተመልከት! አድዋ የኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካዉያን ድል ነው፡፡ ዳሩ ምን ያደርጋል በራሳችን መድመቅ አንወድምና ቴሌ በስልካችን ከሚልከው ተለመደ ‹የእንኳን አደረሳችሁ!› የሚል መልዕክት፣ ከአባት አርበኞቻችን ሰልፍና ፉከራ፣ እንዲሁም ከአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የዜና ሽፋን የዘለለ ተጨባጭ ነገር መፍጠር አልቻልንም፡፡ ጋዜጠኞቻችን ከአድዋ ድል በላይ ስለ አርሴናል እዉቀት አላቸው፡፡ ከምኒልክ የጦር ጀብዶ በላይ ስለ ሜሲ የኳስ ጥበብ ቢተርኩ አይጠግቡም፡፡ በዚህ ሁኔታችን ከቀጠልን የአድዋ ድል ቀናችንን ዘንግተነው በተቃራኒው የዉጭ ሚዲያዎች የሚያስታውሱን ይመስለኛል፡፡ አድዋ ግን አንድነታችን ምሳሌ ነበር፡፡ እረኛው ከሰላዩ፣ አዝማሪው ከወታደሩ፣ ወጥቤቷ ከወታደሩ፣ ንጉሱ ከህዝቡ ጋር ተግባብቶ ነው ድሉ የመጣው፡፡ እዉነት ለመናገር የአድዋን ቀን ከኛ በላይ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የሚያከብሩትና የሚያስቡት ይመስለኛል፡፡ ለአፍሪካዉያን የነጻነትን ብርሃንን ወገግ ያደረገላቸው አድዋ ነዋ! ጥቁር ህዝብ ነጭን ማንበርከክ እንደሚችል በተግባር ያረጋገጠላቸው አድዋ ነዋ! የታነቁበትን የባርነት ቀንበር ሰንሰለቱን የበጣጠሰላቸው አድዋ ነዋ፡፡ የበትሩ ቀማሽ ጣሊያንም ብትሆን ሳትወድ በግዷ የሽንፈት ካባ የተከናነበችበትን ቀን በፍጹም አትረሳውም፡፡ ተረቱስ ቢሆን ‹‹የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም!›› አይደል የሚባለው፡፡ እኛ ግን በሞቀው ዘፋኞች ነን፡፡ ይሄን ጊዜ ግንቦት ሃያ ቢሆን ኑሮ ህዝቤ ሰንደቅ አላማ እያዉለበለበ፣ ሻማ ለኩሶ ሰልፍ በወጣ ነበር፡፡ የብአዴን ውልደት ቢሆን ኑሮ… የኦህዴድ ልደት ቢሆን ኑሮ… የህወሃት ክብረ በአል ቢሆን ኑሮ… የኢህዴን ትንሳኤ ቢሆን ኑሮ… ከተማው በሙሉ በሰንደቃላማና በባነር… በቲሸርትና በፖስተር በደመቀ ነበር፡፡ በጀት ተበጅቶና ገንዘብ ተዋጥቶ ቅጠሉና ግንዱ… ህንጻዉና መንገዱ ሁሉ ቀለም በተቀባ ነበር፡፡ አየህ! ባናገናዝብ እንጂ ከግንቦት ሃያም…. ከህወሃትም… ከብአዴንም… ከኦህዴድም… ከደህዴንም… በፊት አድዋ ነበር፡፡ በዛሬያችን ህልዉና ዉስጥ ድሮአችን ይቀድም ነበር፡፡ ከዛሬ ፍርክስክስ ማንነታችን የአድዋ አንድነታችን ይገዝፍ ነበር፡፡ አሁን ላይ አገሪቷም ህዝቦቿም ህመምተኞች ሆነናል፡፡ በሽታ ተጠራርቶ ቤቱን ሰርቶብናል፡፡ ድህነት እጅ ወደላይ እንድንል አስገድዶናል፡፡ ከመንገድ ላይ ቅፈላ እስከ መኪና ላይ በድምጽ ማጉያ የተደገፈ ልመና አዲሳችን አይደለም፡፡ ለምንኖርበት ብቻ ሳይሆን ለምንመገብው ምግብ እንኳን ዋስትና የለንም፡፡ ለዚህ ይመስለኛል፡- ‹‹ኑጉ የሚመረት በገዛ አገራችን ሰሊጡ ሚመረት በገዛ አገራችን በጀሪካን ዘይት ፈሰሰ መቅኔአችን፡፡›› ሲል የባህር ዳር አዝማሪ ምሬቱን የገለጠው፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ይቺ ሃገር ሞታ የተቀበረችው የግብረ ገብነት ትምህርትን ከትምህርት ስርዓት ላይ ፍቃ ስታወጣው ነው፡፡ ተመልከት! ግብረገብነት ከጭንቅላታችን ተሟጧል፡፡ መተዛዘን ተዘንግቶ መገዳደል ተበራክቷል፡፡ የሰው ልጅ ክቡር ነፍስ ዋጋው ከሳንቲም ቀሏል፡፡ የሃብታምና የባለስልጣን ልጅ ትምህርት ቤት ያማርጣል፡፡ የደሃ ልጅ ማስቲካ እየሸጠ ለወስፋቱ ማስታገሻ ዳቦ ለመግዛት ሳንቲም ይለቅማል፡፡ አለፍ ሲልም ጎዳና ያድራል፡፡ ተማሪ የእዉቀት አባቱ የሆነውን መምህሩን ያንጓጥጣል፡፡ በህገወጥነት ታላላቆችን ይዘልፋል፡፡ ህገወጥነት እያደገ ሲሄድ ደግሞ በመንግስት ላይ ድንጋይ የሚወረዉረው ትዉልድ ይበዛል፡፡ ይሄ ትዉልድኮ መንገድ ስቷል፡፡ አይነስዉርን መምራት ሳይሆን የመምሪያ ዘንጉን ቀምቶ የሚሮጠው በዝቷል፡፡ ቤርጎ አከራይተኸው አንሶላ ይዞ ይወጣል፡፡ ማድረቂያ ፎጣ አስቀምጠህለት በብርድ ልብስ ገላውን የሚያዳርቅ፣ ቆሻሻ እግሩን በአንሶላ የሚጠርግ ወጣት እየተፈጠረ ነው፡፡ አየህ… ግብረገብነት ሲጠፋ ሀገር በእጅጉ ትባልጋለች፡፡ መረን የለቀቁ ብትን ልጆች ይፈለፈሉባታል›› ፕሮፌሰር ይህንን ሁሉ ርዕሰ ጉዳይ እያነሱ ሲያጫዉቱኝ /እዉነት ለመናገር ዉስጤን ሲያቃጥሉኝ ቢባል ይቀላል፡፡/ ቆይተው ለመለያየት ከመቀመጫችን ስንነሳ የምሳ ሰዓት አልፎ ስምንት ሰዓት ሊሆን ጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ቀርተዉ ነበር፡፡ **** ፕሮፌሰር ሙሴን ተሰናብቼ የዩኒቨርሲቲውን ግቢ ለመልቀቅ ስንቀሳቀስ ሰዉነቴ ደንዝዞ ጭንቅላቴ ብቻ የዶክተርን ንግግሮች ያንሸራሽራቸው ነበር፡፡ ጥቂት ሜትሮችን እንደተጓዝኩ ፕሮፌሰር ‹‹ሲሳይ›› ሲሉ ጠሩኝ፡፡ ዝም አልኳቸው፡፡ ‹‹ሲሳይ…!›› ድምጻቸው ይበልጥ አስተጋባ፡፡ ዞር ብየ ተመለከትኳቸው፡፡ ሁኔታየን አይተው ፈገግ አሉ፡፡ ከዚያም ‹‹…ይህንን ሁሉ ከዚያም ከዚህም ቀላቅየ የነገርኩህ በሃገራችን ሁኔታ እየተብሰለሰልክ ሰላምህን እንድታጣ ሳይሆን አንተ ተቀይረህ ሰው እንድትቀይር ነው!›› ብለዉኝ ፊታቸውን አዙረው በቀጭኗ አስፋልት መንገድ ወደ መምህራን ሰፈር አቅጣጫ ገሰገሱ፡፡ ወይ ፕሮፌሰር! ሰላሜን ካሳጡኝ በኋላ ‹‹በንግግሬ እየተብሰለሰልክ ሰላምህን እንድታጣ አይደለም፣ ተቀይረህ ሌሎችን እንድትቀይር ነው!›› ይሉኛል እንዴ? በአፍዝ አደንግዝ ሟርት እንደተያዘ ሰው ብቻየን እያወራሁ ቤቴ ደርሼ አልጋየ ላይ ጋደም ብልም የፕሮፌሰር ንግግሮች ከጭንቅላቴ ሊፋቁ አልቻሉም፡፡ ወዲያው እንዴት ባለ መንገድ እራሴን ለዉጬ ሌሎችን መቀየር እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ በፕሮፌሰር ምክር መሰረት መጀመሪያ የለውጡ መሪ መሆን ያለብኝ እኔ ነኝ፤ ቀጥሎ ሌሎች ወጣቶችን መቀየር፡፡ የት ያሉ ወጣቶችን ነው መቀየር ያለብኝ? ትምህርት ቤት? ዩኒቨርሲቲ? ወይስ ጫት ቤት? ቅድሚያ ጫት ቤት የተቀመጡ ወጣቶችን ለመለወጥ በማሰብ በሰፈራችን ወደሚገኝ አንድ ጫት ቤት ገሰገስኩ፡፡ ከቦታው ስደርስ ሴቶቹም ወንዶችም ጫት እየቃሙ ነበር፡፡ የተወሰኑት ጥንድ ጥንድ ሆነው ጨዋታ ይዘዋል፡፡ ሌሎች ደግሞ በራሳቸው አለም ዉስጥ ናቸው- አድማሱን እያዩ በተመስጦ ያስባሉ፡፡ ጥቂቶች በቁራጭ የሲጋራ ወረቀት ላይ የሆነ ነገር ይጽፋሉ፡፡ በአጠቃላይ ሁሉም ምርቃና ላይ ናቸው፡፡ የመረቀነን ሰው ደግሞ እንዲሁ በደረቁ ማናገር ከባድ ነው ብየ አሰብኩ፡፡ ወዲያው ‹‹የሰዉን አስተሳሰብ ለመለወጥ መጀመሪያ ከእነሱ ጋር ተመሳስለህ ነው›› ብሎ አንድ ወዳጄ የነገረኝ አባባል ትዝ አለኝ፡፡ አስተናጋጇ ወዲያ ወዲህ ትመላለሳለች፡፡ የጎደለው ላይ ጎደሎውን ፈጥና ትሞላለች፤ እንደ ታዳሚው ፍላጎት ጫትና ሲጋራ ዉሃና ለስላሳ ታድላለች፡፡ እዚያ ቤት ካሉት ሰዎች ዉስጥ እሷ ብቻ ናት ጫት የማትቅመው፡፡ በምልክት ወደኔ እንድትመጣ ጠራኋት፡፡ ‹‹ምን ልታዘዝ?›› አለችኝ ‹‹መቶ ግራም ጫትና አምስት ፍሬ ሲጋራ!›› አልኳት፡፡ የለውጥ ሃሳብ የሚገኘው ከጫት እና ከሲጋራ ነው የሚል ሃሳብ ዉስጤ ሹክ ሲለኝ፡፡ ትዉልዱ እንዲህ ሆኗል… እኔ ደግሞ የትዉልዱ አንድ አካል ነኝ፡፡ የከሸፈው ትዉልድ!

Comments

Popular posts from this blog

ገረዲቱ - ኦርቶዶክሳዊ ትምህርት

የህልሜ ጓደኛ 3

የህልሜ ጓደኛ 2