አትነካኪኝማ
ተይ አትነካኪኝ አትቀስቅሽኝ እቴዋ ትዝታችን ላይ ነው የተኛሁ የጊዜን ምንጣፍ አንጥፌ አትነካኪኝ ልረፍበት አትቀስቅሽኝ ከእንቅልፌ አትወስዉሽኝ እቴዋ ከነካካሽኝማ በጊወርጊስ በተስኪያን በመንገዱ ዳር አልፌ አደባባዩን ዙሬ በዘንባባው ጥግ ታጥፌ አንድ ጊዜ ካፌው በር ላይ ሌላ ጊዜ መናፍሻው እዚያ ከወፎች መንደር እዚያ ከፍቅር ዋሻው መናፈሻው… አስታውስሺው? ሌላ ጊዜ ከሰፈርሽ ሌላ ጊዜ ከሰፈሬ ከተሰገሰገበት ሚስጥርሽና ሚስጥሬ ሌላ ጊዜ በጸሃዩ ሌላ ጊዜ በምሽቱ መጨለሙን መች አስቤው ልቤ ያለ ከመንጋቱ፡፡ ታስታዉሻልሽ ግን… ከጠዋቷ ጸሃይ ጋር እኩል ነበር ምጠብቅሽ ልቤን ቅልጥ የምትለው አንድም በብርሃኗ አንድም ደግሞ በፈገግታሽ፡፡ አትነካኪኝ እቴዋ ከነካካሽኝማ ትናንትናን እያሰብኩ ነገየን እየረገጥኩ ህልሜን እየደፈጠጥኩ ተስፋየን እየገደልኩ በሃሳብ ሽምጥ ግልቢያ ትናንት ላይ እደርሳለሁ ያንን ጊዜ አነሳለሁ ድሮአችንን አነግሳለሁ አሁኔን እቀብረዋለሁ በዛሬ ጀምበር ላይ ቆሜ ትዝታሽን እኖራለሁ፡፡ አትወስዉሽኝ አለሜ ዛሬ ላይ ተገትሬ ልጅነታችንን ያሰብኩለት ያ መነፋፈቃችን ያ መፈላለጋችን የመዋደዳችን ግለት በጊዜ ምድጃ ላይ ቀናትን እያነደደ ትዝታ የሚባል ጉቶ እቶኑ ዉስጥ እየማገደ የፍቅርን ፍም እሳት ያፈልቃል ደክሞት የተኛን ገላ፣ የተኛን ልብ ያሞቃል፡፡ አታስታዉሽኝ እቴዋ አታሰሚኝ ድምጽሽን አታሳይኝ ከንፈርሽን አታስታዉሽኝ ፈገግታሽን …ጥርስሽን ያሰብኩለት ተደርድረው በመደዳ ከህሌናየ ላወጣሽ ለራሴ የማልኩትን ቃልን ነው የምከዳ!!! ተይ አትነካኪኝማ ተይ አትወስዉሺኝማ ተይ አትቀስቅሺኝማ ተይ ተይ ተይ ...